ይህን የዐደራ መልእክት ለጠ/ሚ ዶክተር ዐቢይ አድርሱልኝ! (ነፃነት ዘለቀ – አዲስ አበባ)

0
24

ነፃነት ዘለቀ (አዲስ አበባ)

PM Abiy Ahmed to the people of Ethiopia.

ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያ ሀገራችን እያገባደደችው ከነበረው ተያይዞ ውድቀት እንድትላቀቅ ፈጣሪ ፈቅዶ የላከልን የለውጥ ምክንያት እንደሆነ በበኩሌ ምንም ጥርጥር የለኝም – ተወደደም ተጠላ ይህን አለማመን ውለታቢስነት ይመስለኛል፡፡ ከዘመናት ችግሮቻችን መጥነን (መክበድ) የተነሣ እግዚአብሔር ይህን ብላቴና አንስቶ ሙሤ እስራኤላውያንን ከፈርዖን የግፍ አገዛዝ ነፃ እንዳወጣ ሁሉ እኛንም ፈጣሪያችን ከምድራውያን አጋንንት ከወያኔዎች ነፃ ሊያወጣን በመፈለጉ በዚህ ልጅ ተመስሎ መጣ – የብዙ ጸሎትና የብዙ ደምና አጥንት ውጤትም ነው፡፡ እርግጥ ነው በምናያቸው አንዳንድ ነገሮች ምሬታችንንና ተቃውሞኣችንን በመሰለን መንገድ ልንገልጽ እንችላለን፤ የሚጠበቅም ነው፡፡ በጭፍን መደገፍ በጭፍን ከመቃወም አይለይምና ከሀገራችን ሽፍንፍን ባህል ወጣ እያልን አካፋን አካፋ ለማለት የሠለጠነውን ዓለም ፈለግ መከተላችን የሚያስመሰግን እንጂ በአንድ ራስ ሁለት ምላስነት የሚያስወቅስ ሊሆን አይገባም፡፡ በእግረ መንገድ ለማስታወስ ያህል – ሙሤ ሕዝቡን ነፃ ሲያወጣ ሁሉ ነገር አልጋ ባልጋ ሆኖለት አልነበረም፡፡ ብዙ ችግሮች ነበሩ፡፡ ሕዝቡ አልታዘዘው እያለ ይናደድና ይበሳጭ ነበር፡፡ ከንዴቱም የተነሣ ከፈጣሪ ያመጣውን የመጀመሪያውን የዐሠርቱ ትዕዛዛት ሠሌዳ (ታብሌት) በቁሙ ለቆት እንደተሰባበረ ይነገራል፡፡ ስለሆነም ዐቢይ ላይና በዐቢይ ዙሪያ የምናስተውላቸውን አንዳንድ የማንረዳቸው ክስተቶች እንደችግር ብንቆጥራቸውና ባፋጣኝ እንዲስተካከሉም የሚሰማንን ብንገልጽ የሚቀየመን ወይም የሚቆጣንና የሚያኮርፈን ሊኖር አይገባም፡፡ በነፃነት ሂደት ብዙ ውጣ ውረድና ብዙ እንቅፋት፣ ብዙ አለመግባባትና ብዙ የጦፈ ውዝግብ መኖሩ ያለ ነውና እየተቻቻልን የተጀመረውን የነፃነት አቀበት እንውጣ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ የለውጡም ኃይል ስል ጆሮዎች ቢኖሩት ድካሙን ቀለል ያደርግለታል፤ አለበለዚያ የአሮጌውና የአዲሱ አቅማዳዎች የወይን ትርክት መደገሙ ነው፡፡ ማድመጥ ማንን ጎዳ?

ወያኔዎች እየተቅበዘበዙ መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ ለውጡን ለመቀልበስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አለመኖሩም ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ የለውጡ ኃይል ሌት ተቀን ነቅቶ መጠበቅ አለበት፡፡ በተለይ የለውጡ አካላት መስለው ሕዝብን በማበሳጨት የቀድሞውን ከፋፋይና ዘረኛ ሥርዓት እንዲናፍቅ ለማድረግ የሚጥሩ ኃይሎችን መከታተል ተገቢ ነው፡፡ የሕዝቡን የዕለት ከለት ኑሮ በማስወደድና የመሠረታዊ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን ዋጋም በማናር እየተጫወቱት ያለው አፍራሽ ተግባር በቶሎ ካልተቀለበሰ ይህ ለውጥ ችግር ውስጥ እንደሚገባ መታወቅ አለበት፡፡ የወያኔ ሰዎች አሁንም በስፋት ሥራ ላይ ስላሉ መብራት በማጥፋት ወይም በማቆራረጥ፣ ውኃን በመዝጋት፣ አማራ ቲቪን የመሳሰሉ የሚጠሏቸውን  የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን አየር ላይ በማስቀረት፣ በየወረዳውና ከፍተኛው ሕዝብን በማጉላላትና የለመዱትን ሙስና የእስትንፋሳቸው መቀጠያ በማድረግ፣ ዜጎች በለውጡ እንዲማረሩ በርካታ ሸሮችን በመሥራት፣ ወዘተ. ሥውር ወያኔያዊ ተልእኳቸውን በመወጣት ላይ እንደሚገኙ የታወቀ ነው፡፡ ተጨማሪ ጥቂት ምሣሌዎችን ተራ በተራ ማየት እንችላለን፡፡

በለውጡ ኃይል ውስጥ ከሚገኙ ባለሟሎች ብዙዎቹ የዱሮው ንጹሕ ባንዲራችን ጋር ጠብ ያላቸው ይመስላሉ፡፡ እሱን ባንዲራ ከያዙ ዜጎች ጋር አምባጓሮና ውርክብ መፍጠርና በሰበቡም ንጹሓን ዜጎችን አስሮ ማሰቃየት የሚቀናቸውና ሰውን የማሰቃየት ሱሳቸው ገና ያልለቀቃቸው አሉ – እነዚህ ሰዎች ጊዜው የሃሳብ ፍትጊያ እንጂ የዱላና የልምጭ እንዳልሆነ ሊነገራቸው ይገባል፡፡ አልሰማም ካሉም ቦታቸውን እንዲለቁ መደረግ አለበት ወይም የመግረፍ ሱሳቸው እንዲበርድላቸው መንግሥት አሮጌ መጋዣና አህያ እየገዛ ያቅርብላቸውና እነሱን ይግረፉ – ( እኔም ጨካኝ ሆንኩ – እነሱስ አለአበሳቸው ለምን ይገረፉ ልጄ!)፤ መተማመንና በሃሳብ ፍጭት መሸናነፍ ካልመጣ በፍራቻና በድብብቆሽ መኖራችን ይቀጥላል፡፡ ለማንኛውም ያን ባንዲራ ሲያዩ ዐይናቸው ደም የሚለብስ ሰዎች አደብ ቢገዙ ጥሩ ነው፡፡ በተቃራኒው ሌላ ባንዲራ ሲያዩ በደስታ ድባብ ተውጠው የሚሆኑትን የሚያጡ አሉ፡፡ ይህ ደግሞ በፈረንጅኛው አባባል double standard ነው፡፡: ብዙ ነገር እየታዘብን ነው፡፡ ሁሉም ይወቀው – ያቺን ንጹሕ ባንዲራ የሚጠላ መጨረሻው በፍጹም አያምርም፡፡ የፈለግኸውን በል – እውነቱ ይሄው ነው፡፡

የኤሌክትሪክ ፍጆታ ላይ የታሪፍ ለውጥ ማድረግ በተለይ አሁን ለምን አስፈለገ? ጭማሪ ይደረግስ ቢባል በኪሎ ዋት ከሃምሣ ሣንቲም ወደ አንድ ብር ከሃምሣ ሣንቲም ማሳደግ ምን የሚሉት ጭማሪ ነው? የ1966ቱ አብዮት የወዲያው መነሻ በአንድ ሊትር ቤንዚን ላይ የተደረገ የአምስት ይሁን የዐሥር ሣንቲም ጭማሪ አይደለም ወይ? የሕዝብ ገቢ በተለይም የተቀጣሪው ዜጋ የወር ደሞዝ ምንም ለውጥ ባላሳየበት ሁኔታ በአንዴ ከመቶ ፐርሰንት በላይ መብራት ላይ መጨመር የጤና አይመስለኝምና ይታሰብበት፡፡ በዚያ ላይ ይህ ጭማሪ የሚያመጣቸው ሀገርንና ሕዝብን የሚጎዱ አሉታዊ ጎኖች ብዙ መሆናቸው ግልጽ ሊሆንልን ይገባል፡፡ በደን ጭፍጨፋ ላይ፣ በቤት ኪራይ ላይ፣ በትራንስፖርት ላይ፣ በሸቀጦች ዋጋ ላይ… እጅግ ዘርፈ ብዙ የጎን ጉዳቶችን ማስከተሉን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ይህን ጭማሪ ማን አፈለቀው?  ለምንና አሁን ተደረገ? ብለን መጠየቅ ይገባናል፡፡

በእውነቱ ይህን ጭማሪ በአሁኑ ወቅት ማድረግ ለውጡና ሕዝቡ ላይ ትልቅ ጦርነት እንደማወጅ ይቆጠራል፡፡ ጥቅም እየጨመረ ይሄዳል እንጂ አይቀነስም፡፡ የዐቢይ መንግሥት በስድስትና ሰባት ወር ውስጥ ማርና ወተት እንዲያዘንብ አይጠበቅበትም፤ ግን ከነበረው ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ያነሰ ሊሆን አይገባም፡፡ አሁን ግን በዚህ ለውጥ ውስጥ ወያኔ ባሠረጋቸው ጀሌዎቹ አማካይነት ብዙ አሻጥር እየተሠራ ነው፡፡ ስለዚህ ፀረ-አሻጥር ኮሚቴ ተቋቁሞ ከሕዝብ ጋር በየጊዜው እየተነጋገረና እየተመካከረ አንዳች አወንታዊ ሥራ ለመሥራት ይሞከር፡፡ አለበለዚያ ዕንባ ሲበዛ ጎርፉን የሚችለው አይኖርም፡፡ የሕዝብን ዕንባ መናቅ ይቻላል፤ የሕዝብን ብሶት ማፈን ይቻላል፤ ወያኔ እንደሚያደርገው ሕዝብን በጥይት እሩምታ እየረፈረፉ “ማስተዳደር” ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከታሪክ የምንማረው ትልቅ ቁም ነገር ይህ ዓይነቱ ልበ-ድፍንነት በመጨረሻው ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን ነው፡፡

ወያኔን በተወሰነ ደረጃ “መታገስ” (መፍራት› ላለማለት ነው) ጥሩ ነው፡፡ ከምንም ተነስቶ ወያኔን የሚያህል ሰው በላ ጭራቅ በዚህን ያህል ደረጃ ማንበርከክ መቻል ራሱ ከፍ ሲል እንደተናገርኩት የነዐቢይን ወደ መድረኩ መምጣት ከምድር ሳይሆን ከሰማይ መሆኑን እንድናምን ያስገድደናል፡፡ ሰይጣን በአንዲት “በስማም” ዐርባ ክንድ እንደሚርቅ ካህናት ሲናገሩ እንደምንሰማው መጋቢት 24/2010ዓ.ም በርቱዕ አንደበት በተጀመረ “ተኩስ” ወያኔ እየተሽመደመደ መጥቶ በጎሬው ውስጥ እንዲደበቅ መገደዱ ከተዓምር ውጪ ሌላ ሊባል አይችልም – አለአንዲት ጥይት፡፡ ይሁንና ሰሞኑን እንደተጀመረው የትግስትን አድማስ በማጥበብ የወያኔን የቅልበሣ ሤራ ማክሸፍ ጊዜ የማይሰጠው አጣዳፊ ተግባር መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ሕዝብ ተስፋ መቁረጥ የለበትምና፡፡ በቃላት ብቻ የሚነገር የተስፋ ዳቦ “ላም አለኝ በሰማይ” እንጂ እውናዊ ጭብጥ ቆሎ ሊሆን አይችልምና የሕዝቡን የዳቦ ርሀብና የዴሞክራሲ ጥማት ለማስወገድ መጣደፍ የወቅቱ ተግባራችን ይሁን፡፡ ጊዜ የለንም፤ ጊዜያችንን ዐረመኔው ወያኔ ቀርጥፎ በልቶታል – 44 ዓመት ከአንድ ማኅበረሰብ ዕድሜ መስረቅ በትንሹ አንድ ተኩል ትውልድ እንደማባከን ነው፡፡

ትግራይ ውስጥ በሥውር ቦታዎች ታስረው የሚሰቃዩ ወንድም እህቶቻችን እንዲለቀቁና አጥፊዎች ወደ ፍትህ አደባባይ እንዲወጡ ብዙ ሥራ መሠራት ይኖርበታል፡፡ እሹሩሩ ይቁም፡፡ ከእንግዲህ ከወሬ ዘመቻ ወደ ተግባር እንዙርና ከድህነት የሚያወጣንን የምርት ዘመቻ እናቀላጥፍ፡፡ በየሚዲያው የሚደረገው ጽንፍ የያዘ የፖለቲከኞች አታካራም ቆሞ ወደ ሀገር ልማትና ብልፅግና በአስቸኳይ እንመለስ፡፡ ስድብና ዘለፋ፣ መጠላለፍና ንትርክ፣ በየጎጥ መቧደንና መቆራቆስ፣ በጎሣና በዘር መከፋፈልና ጥላቻን ማስፋፋት፣ … በአፋጣኝ መቆም አለበት – ለብዙ ዓመታት አየነው – የኋሊት ጎተተን እንጂ አንዳችም አልጠቀመንም፡፡ እስካሁንና አሁን ባለንበት ሁኔታ ከቀጠልን በቆምንበት መርገጥም እየናፈቀን  ካሁኑ በባሰ ቁልቁል ወርደን እንፈጠፈጣለን፡፡

የትምህርት ጥራት ይጠበቅ እየተባለ በድህነት አረንቋ የሚኖሩ መምህራን እዚያና እዚህ ተሯሩጠው የሚያገኟትን ገንዘብ ለመቀማት የመንግሥት ቴክኖክራቶች የሚተገብሩት የግብር አከፋፈል ሥራት እጅግ ኢፍትሃዊ ነው፡፡ አንድ መምህር የሚያገኛት ደሞዝ በጣም አነስተኛና ከወር እወር ቀርቶ ለሦስት ቀናትም የማትበቃ ናት፡፡ ያቺን ለመደጎም ብሎ ከሚሠራበት የትምህርት ተቋም ውጪ በትርፍ ሰዓቱ ልሥራ ቢል ከደመወዙ ላይ ተጨምሮ (በprogressive taxation) በጨካኞች መጋዝ ይበለትና ከመቶ ብር 65 ብር ብቻ እንዲደርሰው ይደረጋል፡፡ ይህ የግፎች ሁሉ ጫፍ ነው፡፡ በመጀመሪያ አንድ ሰዓት ሠርቶ 65 ብር መክፈል ነውር ነው – ሊስትሮና የቀን ሠራተኛ እንኳን ይቺን ብር ይንቋታል፡፡ “መማር ከንቱ” የሚያሰኝ አስቂኝ ክፍያ ነው – አንድ ሽሮ 150 ብር – አንድ ኪሎ ሥጋ 400 ብር – አንድ የድሃ ሸሚዝ 500 ብር – አንድ ሊትር ዘይት ባማካይ 70 ብር በገባበት ዘመን ይህን ገንዘብ ለአንድ መምህር በሰዓት መክፈል ምፀት ነው፡፡ የአሁኑ 65 ብር ከሃያ ዓመት በፊት የነበረውን ሦስት ብር አይሆንም፡፡ ዱሮ በነበረ ደሞዝ የተተከለ የግብር አከፋፈል ሥርዓት አሁን ተግባራዊ ማድረግም አለማወቅ ወይም ግድሌሽነት ነው – 35 ፐርሰንት ግብር ሲደመር 15 ፐርሰንት ተጨማሪ እሤት ታክስ በድምሩ  ከ50 ፐርሰንት በላይ መምህራን ከደሞዛቸው ይቆነደዳሉ፤ ማን ይዘንላቸው? የግብር ማዕቀፎች መሻሻል ሲገባቸው እዚያው ናቸው – ለምሣሌ ትልቁ የግብር ታሪፍ ከ15 ሽህ ብር አካባቢ ደሞዝ ቢጀመርና ከዚያ በታች ባሉት ላይ እየተጠና ሌሎቹ ታሪፎች ቢሆኑ መጠነኛ እፎይታ ይፈጥራል፡፡ የራስን ኑሮ በሙስናና በልዩ ልዩ የጎን ገቢዎች እየደጎሙ የምሥኪን ዜጎችን ደሞዝ በሰበብ አስባብ እየሸረከቱ ባዶ ማስቀረት በምድር ባይሆን በሰማይ ያስጠይቃል፡፡ ይህ መታሰብ አለበት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለአብነት በዓመት በሚሊዮኖች የሚያገኝ ነጋዴ በ tax evasion or tax avoidance እና በማጭበርበር ወይም ከታክስ ባለሥልጣናት ጋር በጥቅም በመሞዳሞድ ወይም በመዋሸትና የሀሰት ሠነዶችን በማዘጋጀት በጣም ኢምንት ግብር ሲከፍል አንድ መምህር በደሞዙ ሥልጣን ስለሌለው በመንግሥት ርህራሄ የሌለው ቢላዎ ተቆራርጦ እንዲደርሰው ይደረጋል – ምሥኪን፡፡ በዚያ ላይ ተሯሩጦ ያቺን ጉድለት እንዳይሞላ ቢላዎው በየሄደበት እየተከተለ ያሳድደዋል፡፡ መንግሥት የት ነው ያለው እንግዲህ?  እውነተኛውን ልጅህን እያሳደድክ የምትቀረጥፍ መንግሥት ሆይ እየሰማኸኝ ነው? “አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ” ነው፡፡

በዚህ አካሄድ የትምህርት ጥራት አይታሰብም፡፡ አንድ ምሁር “አምና እረኞቹ ነበር የመጡት፤ ዘንድሮስ በጎቹ ራሳቸው ናቸው የመጡት” አለ አሉ – የተማሪዎቹን ሁኔታ ታዝቦ፡፡ እንደመምህርነቴ አሁን አሁን ወደ ዩኒቨርስቲ ከሚገቡት አዳዲስ ተማሪዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ይቅርና አፍ በፈቱበት ቋንቋ ራሱ ልትግባቡዋቸው ይቸግራችኋል፡፡ የወያላው ማለቴ የወያኔው ወሮበላ ቡድን ከተሳኩለት ነገሮች አንዱ ትምህርትን በአፍ ጢሙ መድፋት ነው፡፡ `many branched problems (“ዘርፈ ብዙ ችግሮች” ለማለት), the buying government (“ገዢው ፓርቲ/መንግሥት” ለማለት), I doesn’t know[to say – I don’t know], Don’t afraid me [ to mean – Don’t be afraid of me], etc. የሚሉ የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ ምሩቃንን ስንታዘብ ክፉኛ እንዳልደነገጥንና እንዳልተሳቀቅን ሁሉ ዛሬ ዛሬ ያም እንደ ብርቅ እየተቆጠረ የለየላቸው ዱዳ ተማሪዎችን በየክፉሉ እያጎሩ መምህር መመደብ ተጀምሯል – ብዙ ነገሮች የግብር ይውጣ እየሆኑ ነው፤ ደናቁርት ደናቁርትን “እያተስማሩ” ሀገር የማይማን መፈንጫ ሆናለች – ዕውር ዕውርን ቢመራው ውጤቱ ተያይዞ ገደል መሆኑ አይካድም – ሀገራችን ውስጥ እየሆነ ያለው ይሄው ነው፤ በሁሉም መስክ ነው ታዲያ – በትምህርቱ ብቻ እንዳይመስልሽ/እንዳይመስልህ፡፡ ኢትዮጵያየ – መጨረሻሽ ምን ይሆን? ትነሻለሽ ወይንስ እንደተኛሽ ትቀሪያለሽ?  ቀኑ ራቀብኝ፡፡ አዎ፣ የዘር ፖለቲካና የነሆድ አምላኩ የአገዛዝ ቅኝት መጨረሻው ይህ ነው፡፡ የኔ ነው የምትለው ነገር እንዳይኖር፣ እኛነት በእኔነት እንዲተካ፣ መተሳሰብና መተዛዘን በጭካኔ እንዲለወጥ…  የዘረኝነትና የአፓርታይድ ሥርዓት ያላቸው ሚና ትልቅ ነው፡፡

ከውጭ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ የተጣለው የግብር መጠን ሲሰሙት ራሱ ይሰቀጥጣል፡፡ በሁለት መቶ ሽህ ብር ለሚገባ መኪና ቀረጡ ከብር አንድ ሚሊዮን በላይ መሆኑ ሲነገርህ የት እንዳለህ በመደነቅ አፍህን ይዘህ ትቀራለህ፡፡ ብዙ ነገሮች ይገርማሉ፡፡ ኑሯችን ሜካኒካዊ እንጂ የሰው ሕይወት ያለበት፣ የሚያስብ ሰው የሚሣተፍበት፣ መደማመጥና መግባባት የሚስተዋልበት፣ በዜግነትና በሰውነት መከባበር የሚታይበት … አይመስልም፤ አይደለምም፡፡ ሮቦቲክ ሕይወት፣ የዞምቤዎች ሀገር፣ የሰው መሳይ አሻንጉሊቶች ግዛት ከመሆን እናድናት – ኢትዮጵያ ሀገራችንን፡፡ የሚሸሹዋት ሳትሆን የሚቀርቧት፣ የሚጠሏት ሳትሆን የሚወዷት፣ የሚሸጧት ሳትሆን አክብረው የሚይዟት ሀገር አንድትሆን ብዙ መሥራት ይኖርብናል፡፡ በተለይ በተለይ ለሀገር ገምቢዎች መምህራን የተሰጠው ትኩረት እጅግ አናሳ ነውና የትምህርት ጥራታችን አሁን ካለውም በከፋ ሁኔታ ወርዶ ስሙን መጻፍ የማይችል የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ ተመራቂዎችን ከማምረታችን በፊት በዚህ ጽሑፌ ውስጥ የጠቀስኳቸው ችግሮች ነገ ዛሬ ሳይባል ይፈቱ፡፡ ችግርን ማቆር/ማከማቸት ቀላል ነው፡፡ ችግሮችን ጆሮ መንፈግ ቀላል ነው – የለመድነውም ነው፡፡ ነገር ግን የዞረ ድምሩ ከባድ  ነው – በተግባርም እያየነው ስለሆነ፡፡ “ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል” ይባላል፡፡ ኑሮው የተጎሳቆለ መምህር ክፍል ውስጥ ገብቶ ፊደልን ከማስቆጠር ይልቅ የራሱን ችግሮች በመቁጠር ሰውነቱ ተማሪዎች ፊት፣ አእምሮው ግን በችግሮቹ ጓዳ ውስጥ ነው የሚገኙት፡፡ ኢትዮጵያን እንደገና ጠፍጥፎ ለመሥራት የተነሣ ወገን ዙሪያ ገባ ችግሮቿን በማጤን በቶሎ መፍትሔ ይፈልግ፡፡ ጥሩ ጅምሮች እየታዩ ነው፡፡ ዘለቄታ እንዲኖራቸውና በስፋት እንዲቀጥሉ ግን ጥረቱ ይቀጥል፡፡ እነዚህ መዥገሮች ተለቅመው ጥግ ጥግ ከያዙልን ከዚያ በኋላ ያለው ብዙም አያስቸግርም፡፡ ቁልፍ ችግሮቻችን እነሱ ናቸው፡፡

በየቢሮው ተወትፎ ኑሮን እያጦዘ የሚገኝ አስመሳይ የወያኔ ተላላኪና አሻጥረኛ ሁላም ይመንጠር፡፡ ዘመድ መስሎ ከሚሸጠን ከይሲ እንጠንቀቅ፡፡ ወያኔ ጭንቅላቱ መቀሌ ውስጥ ቢሆን ጭራውና ረጃጅም እጆቹ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥትና በመላው ዓለም ዙሪያ ሊሆኑ እንደሚችሉ እንረዳ፡፡ “ገንዘብ የተሸከመች አህያ” ደግሞ “የማትደረምሰው ምሽግ የለም፡፡” ገንዘባቸው እስኪያልቅ ገና ብዙ ነገር ይሞክራሉ፡፡ ሰዎቹ እልህ ውስጥ ናቸው፡፡ ሰዎቹ የሚደፍረን የለም ብለው ያምኑ ስለነበር ባላሰቡት ሁኔታ ከነበሩበት የእርዚቅ ባህር በመባረራቸው እጅግ ከንክኗቸዋልና ያቺን ቦታ ለማግኘት የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም፤ ከብልጣብልጥነታቸው በተጓዳኝ ንክር ያሉ ጅሎችም በመሆናቸው ተስፋ መቁረጥ የሚባል አያውቁም – ማይማን ደግሞ በቀላሉ ተስፋ አይቆርጡም፤ በቂም በቀልና በጥላቻ የታወረ፣ በዚያ ላይ በዘረኝነት ስካር ናላው የናወዘ ማይም ደግሞ የባሰበት ደንቆሮ ነውና ይህን መሰሉን “ሰው” በጣም መጠንቀቅ ተገቢ ነው፤ ስለሆነም ወያኔዎችን በሩቅ መያዝ፣ መቆጣጠርና እንዳበደ ውሻ ሲወራጩ ብዙ ሰው ለክፈው ጉዳት እንዳያደርሱ መርዛቸውን በብልኃት ማርከስ ተገቢ ነው፡፡

“በፋሲካ የተቀጠረች ገረድ ሁልጊዜ ፋሲካ ይመስላታል” ይባላል፡፡ በመድፍና በታንክ ዘመን ጭንቅላታቸው ውስጥ ገብቶ የመሸገ የአሸናፊነት አባዜ አሁንም እየወዘወዛቸው መከራቸውን ያያሉ፤ አሸናፊነት ማለት ለነሱ በጥይት ብቻ ይመስላቸዋልና የአሁኑ የነዐቢይ አሸናፊነት ለነሱ የሚዋጥላቸው አልሆነም – They are suffering from the disbelief they are immersed in. ሁሌ እንዳሸነፉ፣ ሁሌ እንደበለጡ፣ ሁሌ እንዳጭበረበሩ የሚኖሩ ይመስላቸዋል፡፡ የጊዜን፣ የሁኔታዎችንና የቦታን ለውጦች የማያውቁ እንደተባለውም የደነዘዙ የቀን ጅቦች ናቸው፡፡ ከነሱ መለወጥን የሚጠብቅ ካለ ደግሞ የመጨረሻው ጅል ነው፡፡… ለማንኛውም ሰሚ ጆሮ ይስጠን፡፡ አሜን፡፡

netsanetz28@gmail.com)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here