የዲያቢሎስ ጂራት (ከአንተነህ መርዕድ)

0
15

ከአንተነህ መርዕድ

Ethiopia's TPLF/EPRDF officials

ትናንት በተለቀቀው ዶኪመንተሪ የብዙ ሰው ስሜት እንደተነካ መገንዘብ ይቻላል። ኢትዮጵያ ባለፉት አርባ ዓመታት በተለይም ደግሞ በሃያሰባቱ የወያኔ አገዛዝ በዓለም ዘግናኝ ተብሎ የሚታሰብ ወንጀል ሁሉ ተፈፅሞባታል። አሁንም ያ ወንጀል አላቆመም። አዲስ የሆነው ዓለም በተለይም ኢትዮጵያውያን አናይም፣ አንሰማም፣ አናውቅም፣ አንናገርም ብለን ወስነን ስለነበረ ብቻ ነው። በተለይ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ጋዜጦች፣ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ሬድዮኖች፣ ውጭ የሚሰራጩ ሚድያዎች ሌት ተቀን ሲናገሩ በዚህም ግፍ ሲደርስባቸው አናውቅም አንሰማም ብለን ቆይተናል። አሁን ለፖለቲካ ፍጆታም ይሁን ለሃቅ ተብሎ ትናንት በነዚህ ተሰቃዮች ላይ ዶኪመንተሪ ሲሰሩ የነበሩ የመንግሥት ሚድያዎች ሲነግርሩን ዕውነት ዛሬ ብቻ እንደተገለጠ መጮሁ የእኛን መደንዘዝና ሰለባነት ያጋልጥ እንደሆነ እንጂ ነገሩማ የዲያቢሎስን ጅራቱን ብቻ ነው እንድናይ የተደረገው ፈረንጆች (Tip of the iceberg) እንዳሉት። ህወሃት የሰራትን ትንሿን ሃጢያት ሰምቶ “ከእኔም የሚበልጥ አለ እንዴ?” ብሎ ሰይጣን አፉን ያዘ አሉ። ሰይጣንም የኢትዮጵያ ህዝብም አፋችሁን አትያዙ! የዲያቢሎስን የጅራቱ ጫፍ ነው ያያችሁት። አስቀያሚውና ግዙፉ አካሉን ለማየት ሳትደናገጡ ጎትቱት! ሁለመናውን በግልፅ እንየው! ዳግም በዚች ምድር ኢትዮጵያ እንዳያቆጠቁጥ እንቅበረው። ዓለምም ልጆቻችንም ይማሩበት። በይፋ ይጋለጥ። ለቂም ለበቀል ሳይሆን ለስርየት፣ ለትምህርት።

ዛሬ ማልዳችሁ የባነናችሁ የምትመስሉ ጎጠኞችም ህመሙ የሁላችን ስለሆነ የእናንተ ዓላማ ማስፈጸምያ ለማድረግ አትሯሯጡ። ይህንን ስልት ወያኔ “የቀይ ሽብር ሰለባዎች” ብሎ ምን እንደሰራ ከሃያ አምስት ዓመት በፊት ያደረገውን አንረሳም።

ይህንን መጋለጥ ከትግራይ ህዝብ ጋር ልታያይዙት የምትሮጡ “ተጋሩ” ነን ባዮችም ሆናችሁ ከሌላው ቋንቋ ተናጋሪ የተጠለላችሁ መሰሪዎች ይህ የምታተርፉበት ቢዝነስ መሆኑ ቀርቷል። ወንጀሉን የፈፀሙት አብዛኞቹ ትግርኛ ተናጋሪ አረመኔ ህወሃቶች፣ አማርኛ ተናጋሪ ሞሰብ ላሽ ባንዶች፣ ኦሮምኛ ተናጋሪ ድኩማን ካድሬዎች ሁሉ የሚናገሩትን ቋንቋ አይተን ብሄረሰባቸውን ወንጀለኛ የሚያደርግ የደቦ ፍርድ ውስጥ አንገባም። እያንዳንዱን ወንጀለኛ እንደግለሰብ እናየዋለን ሲጠየቅም እንደግለሰብ ነው መሆን ያለበት። እንደቡድን ተደራጅተው የፈፀሙትም ወንጀል በቡድን ይጠየቁበታል።

አብዛኛውን የዘረፉትና ወንጀል የፈፀሙት መሀል አገር ሆኖ ዋና ተጠያቂ አረመኔዎች ትናንት ዞረው ያላዩትን የትግራይ ህዝብ መደበቂያ ሲያደርጉት “መሃላችሁ የተደበቁ ወንጀለኞች የእናንተ አይደሉም፤ እናንተንም አይመስሉም፣ የዘረፉት የገደሉት ታሪካችሁንና ክብራችሁንም ነው” ብለን መንገር፣ የትግሉ አካል እንዲሆኑ መደገፍ፣ የጥፋቱ ሰለባ እንዳይሆኑ መከላከል ኢትዮጵያዊ ግዴታችን ነው።

ሁላችንም ሰከን እንበል። ወንጀለኞችን የንምናጋልጠውን ያህል ዳግም በዚች አገር ወንጀለኛና ተበቃይ ትውልድ እንዳይከሰት መሰረት ለመጣል፤ ፍትህ እንዲገኝ ዴሞክራሲ እንዲያብብ፣ ተቋማትን መገንባትና ማጠናከር ላይ እንረባረብ። ኤርምያስ እንዳለው ክሩ መተርተር ጀምሯል። መጎተቱን እንቀጥል። ስሜታዊነት የትም አያደርሰንም። ስክነት ካለፈው ስህተታችን ተምረን ወደፊት የምንሄድበትን የሰላምና የፍትህ ጎዳና ያሳየናል። በስሜት ከታወርን ግን ተመልሰን እዚያው ራሳችንን እናገኘዋለን። ቀለበቱን እንስበር። ወደፊት እንራመድ። የተነገረንና የምናውቀው በጣም ትንሹን ነው። ግዙፉን እውነት ስናውቅ ሳንደናገጥ ለመቀበልና ፍፃሜውን ለማሳመር እንዘጋጅ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here