የዕለቱ ዜናዎች

0
78

1. በሲዳማ ዞን በተለያዩ ከተሞች ትላንት በተነሳው ግጭት በትንሹ ሶስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ። በሀዋሳ አንድ ሰው ሲሞት በይርጋለም ሁለት ሰዎች መገደላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። የክልል ጥያቄ በወቅቱ ምላሽ አላገኘም በሚል የተነሳው ብጥብጥ በተለይም በአለታወንዶ፡ ለኩ፡ ይርጋለም፡ ጩኮና ሀገረሰላም ከፍተኛ ዝርፊያ እንዲፈጸም ያደረገ ሲሆን በህይወት ላይ ጉዳት ያደረሱ ጥቃቶችም መፈጸማቸው ታውቋል።

2. የሲዳማ የክልል ጥያቄን ተከትሎ ውጥረት ካነገሰባቸው አከባቢዎች ግንባር ቀደም በሆነችው የሀዋሳ ከተማ ትላንት የጀመረው አለመረጋጋት ያዝ ለቀቅ እያደረገው ቀጥሏል። በከተማዋ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፌደራልና የመከላከያ ሃይል በመግባት ጸጥታውን እያስጠበቀው መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመልክታል። በከተማዋ ከቅዱስ ገብርዔል በስተሰሜን ያለው ክፍል በአንጻራዊ መልኩ ሰላማዊ ሆኖ የዋለ ሲሆን በአላሙራ፡ አቶቴ፡ ሞኖፖልና በመሳሰሉት የከተማዋ ክፍሎች የተኩስ ድምጽ ጭምር ያለበት አለመረጋጋት መከሰቱን ነዋሪዎች በዕለቱ ገልጸዋል። የአንድ ሰው ህይወት የጠፋውም በዚሁ የከተማዋ ክፍል መሆኑ ታውቋል።

3. ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሲዳማ የክልል ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ የሲዳማ ሚዲያ ኔትወርክ አመራሮችና የእንቅስቃሴው አስተባባሪዎች በመታሰር ላይ መሆናቸው ተገለጸ። በእስከአሁን አራት የእንቅስቃሴው አስተባባሪዎች የታሰሩ ሲሆን ሶስቱ የሲዳማ ሚዲያ ኔትወርክ አመራሮችና የቦርድ አባል መሆናቸው ታውቋል። የሲዳማ የመብት ትግል ተሟጋች አክቲቪስት ያሬድ እስጢፋኖስ ወጣቱ የህበረተሰብ ክፍል በመረጋጋትና በትዕግስት መጠበቅ እንዳለበት በመግለጽ ጥሪ አድርጓል። ጥቃት እየተፈጸመ ያለው በሲዳማ ብሄር ተወላጆች ላይም ጭምር ነው የሚለው አክቲቪስት ያሬድ የይርጋለም ከተማ ከንቲባ መኖሪያ ቤት መቃጠል ጥቃቱ በማንነት ላይ ያተኮረ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው ይላል።

4. በሌላ በኩል የሲዳማ ዞን አስተዳደር አለመረጋጋቱ በአስቸኳይ እንዲቆም እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። በተለያዩ የዞኑ ከተሞች የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማስቆም የጸጥታ መዋቅሩ በሙሉ ሃይሉ መንቀሳቀሱን የዞኑ አሰተዳደር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ለኢሳት ገልጸዋል። ሃላፊው አቶ ገነነው አበራ ትላንት ለኢሳት በሰጡት ቃለመጠይቅ የምርጫ ቦርድ ውሳኔን በትዕግስት መጠበቅ ብቸኛው መፍትሄ በመሆኑ የሲዳማ ወጣቶች እንዲረጋጉ ጥሪ አድርገዋል። በየቦታው በሚታየው አለመረጋጋት ውስጥ ስውር እጆች አሉበት ያሉት አቶ ገነነ እነዚያ እጆች የእነማን እንደሆነ ከመጥቀስ ተቆጥበዋል። አሁን ሁኔታዎች እየተረጋጋኑ ነው በለዋል የሲዳማ ዞን አስተዳደር ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ገነነ አበራ።

5. ሲዳማ ትግል አባት በመባል የሚታወቁትና የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ሲ አን መስራችና ለረጅም ዓመታት በመሪነት የቆዩት የአቶ ወልደአማኑዔል ዱባል ልጅ አቶ ደጀኔ ዱባለ፡ በሀዋሳና በተለያዩ ከተሞች እየተደረገ ያለው አመጽ የሲዳማን ህዝብ የሚወክል አይደለም አሉ። የሲ አን የቀድሞ አመራር አባል የነበሩት አቶ ደጀኔ ወልደአማኑዔል ለኢሳት እንደገለጹት በሰው ህይወትና በንብረት ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት በአስቸኳይ መቆም አለበት። መንግስት ስርዓትና ህግ የማስከበር ሃላፊነቱን እንዲወጣም አቶ ደጀኔ ጥሪ አድርገዋል።

6. ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ሰመጉ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ አሣሣቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ሲል መግለጫ አወጣ። ትላንት በአዲስ አበባ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጠው የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ሰብዓዊ መብቶች አያያዝን ለማሻሻል ተጀምሮ የነበረው ተስፋ ሰጪ እርምጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲሸረሸር ቆይቶ፡ አሁን አሣሣቢ ደረጃ ደርሷል ብሏል። የሰመጉ ዳይሬክተር አቶ አመሀ መኮንን ለኢሳት እንደገለጹት ዜጎች በፈለጉበት የሃገራቸው አካባቢ ኑሯቸውን የመመስረት እና በሰላም የመምራት መብታቸውን ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተቱ ድርጊቶች መከሰታቸውና በአጠቃላይ በሀገሪቱ ወደ ሦሥት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ሁኔታውን አሳሳቢ አድርጎታል። ባለፉት አስራ ሁለት ወራት የተፈጸሙ ዋና ዋና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመዘርዘርም መንግስት ህግና ስርዓትን በማስከበር አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈልግ አቶ አመሀ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔን መግለጫ መነሻ አደርገው ጥሪ አቅርበዋል።

7. በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የህሊና እስረኞች እንዲፈቱና እስርና ወከባው እንዲቆም በመጠየቅ የተቃውሞ ሰልፍ እዚህ ዋሽንግተን ዲሲ ተደርጓል። በትላንትናው ዕለት በዋሽንገተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደጃፍ በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ የባህርዳሩ የባለስልጣናት ግድያ በገለልተኛ አጣሪ አካል እንዲመረመር፡ በዚሁ ምክንያት የተጀመረው የጅምላ እስር እንዲቆም፡ አሁንም በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞችና የፓለቲካ መሪዎች እንዲፈቱ ተጠይቋል። ራሱን የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት በሚል የሚጠራው ስብስብ አመራር አባላት ላይ የተፈጸመው እስር የበቀል እርምጃ ነው በሚል ኢትዮጵያውያኑ ሰልፈኞች ተቃውሞ አቅርበዋል። በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ በመከላከያ ሰራዊት ጀነራል የቀረበውን ዛቻና ማስፈራሪያ ሰልፈኞቹ አውግዘዋል። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ለሰልፈኞች በድምጽ የተቀዳ መልዕክት ማስተላለፉም ታውቋል። ሰልፈኞቹ የኢትዮጵያ መንግስት እያካሄደ የሚገኘው አፈና እንዲቆም መጠየቃቸውንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

8. የሶማሌ ክልል መንግስት ከ3ሺህ በላይ ህገወጥ መሳሪዎችን በቁጥጥሩ ስር ማድረጉን አስታወቀ። በርካታ መትረየሶችችን ጨምሮ በቁጥጥር ስር የዋሉት የጦር መሳሪዎች በድንበር በኩል ከየመንና ከሶማሊያ የገቡ መሆናቸውን የክልሉ የሰላምና ደህንነት ቢሮ ገልጿል። የቢሮው ሃላፊ አቶ አብዲ አዲል ከኢሳት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት ባለፉት ከአንድ ወር በፊት የክልሉ ምክር ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል በወሰደው ድንገተኛ ፍተሻ ከተለያዩ ከተሞች ህገወጥ የጦር መሳሪያዎቹ ሊያዙ ችለዋል። በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በተካሄደ የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባም ከ200 በላይ የዞንና የወረዳ አመራሮች መባረራቸውን አቶ አብዲ ገልጸዋል። በሌላ በኩል በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ጋባዥነት የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፋ ኡመር መሀመድ ወደ አማራ ክልል በዛሬው ዕለት እንደሚገቡ ተገለጸ። የሁለቱ ክልሎች የጋራ መድረክ በባህር ዳር ከተማ መዘጋጀቱም ታውቋል።

9. ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል መንግስት በዛሬው ዕለት ባህር ዳር ለሚገባውና በሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ኡመር መሀመድ ለሚመራው የሶማሌ ክልል የልዑካን ቡድን ደማቅ አቀባበል እንደሚያደርግ አስታውቋል። የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ አሰማከኝ አስረስ ለኢሳት እንደገለጹት ኢትዮጵያዊ አንድነትን በቃል ሳይሆን በተግባር ላስመሰከሩት የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ኡመር መሀመድና ለልዑካን ቡድናችቸው በዛሬው ዕለት ደማቅ አቀባበል ይደረግላቸዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here