“የኦቦ ዳውድ ኢብሳ ነገር?…” (ጌድዮን በቀለ)

0
101

ጌድዮን በቀለ
Gedionbe56@yahoo.com

Dawd Ibsa, Oromo Liberation Front (OLF) leader.

Dawd Ibsa, Oromo Liberation Front (OLF) leader.

ኦቦ ዳውድ “ነፃ ግዛታችን“ በማለት በሙሉ ልብና በግልጽ ቋንቋ የነገሩን በሳቸው የሚመራው ኦነግ የመንግስትን መዋቅር ሙሉ በሙሉ አፈራርሶና ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ በማድረግ የራሱን መስተዳድር የተካበት በሁለመናው ኦነግ ብቻ የሚያስተዳድራት ወይም የሚያዝባቸው መንደሮች፤ ከተሞች፤ ወረዳዎች አሉት ማለታቸው ነው። እርግጥ በንግግራቸው ያልገለጡልን እንዲህ ያለው ግዛት የተገኘው ከለውጥ በፊት ነው? በኋላ? የሚለውን ብቻ ነው።

በግልጽነት ረገድ “ለውጥ አራማጁ መንግስትም “ ቢሆን ከመታማት አይድንም። በተለይ ከባለነፍጥ አንጋቢ ተቃዋሚዎች ጋር የተደረገውን ድርድር አስመልክቶ ከጅምላ መግለጫ የዘለለ ስለታጣቂ ሰራዊታቸው እጣ ፈንታ፤ ይንቀሳቀሱበት ስለነበረው አካባቢ ህዝብና የቡድኖቹ ግንኙነት ጉዳይ ፤ ከሁሉም በላይ በነፍጥ አንጋቾቹ ሙሉ ቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ግዛቶች ስለመኖር አለመኖራቸውና ይህንንም አስመልክቶ ስለተደረሰበት ስምምነት በግልጽ ሁለቱ ተስማሚ ወገኖች በጋራ ይፋ ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር። ይሄው የሰሞኑ የተዘበራረቀ መግለጫ የዚህ ክፍተት አንዱ ማሳያ ነው።

ያም ሆነ ይህ፤ ውስጥ-ውስጡን ሲቦካ የከረመው የኦቦ ዳውድ ኢብሳ -ኦነግ የሾርኒ ማንነት ወግ በራሳቸው አንደበት በጠራራ ጸሀይ ወጥቶ ተሰጣ፤  ባንድ በኩል እሳቸው የነገሩን “ነፃ ግዛት” እውን ከነበረ ውነቱ ሲገለጥ መንግስት ከሰላም ጥሪው በፊት የነፃ ግዛት ባለቤትነት ጥያቄ ያላቸውን ባለሰራዊት ድርጅቶች ያስተናገደበትን አግባብ ይፋ እንዲያደርግ የሚያስገድድ ስለሆነ “እሰይ! ይበጅ! “ ሊባል የሚገባው ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንደውነት የተነገረው ቅዠት መሰል ንግርት “ፈጠራ” ሆኖ ከተገኘ፤ አፍን ሞልቶ በድፍረት መናገር እንደነውር ወይም ጸያፍ ቃልነት መቆጠር ያበቃበት ጊዜ ላይ መድረሳችንን በማመላከቱ አስደንጋጭና አሳሳቢ ያደርገዋል። ለምን ቢባል “በመንደር ሽፍትነትና በነጻ አውጭ ሽምቅ ተዋጊነት “ መሃከል ያለው ከተራራ የገዘፈ ልዩነት ድንበር ፈርሶ መቀላቀሉ የማያስጠይፍበት ጊዜ ሆኖ በመገኘቱ ነው።

ሌላው ስለ ኦቦ ዳውድ አስደማሚ መግለጫ ጥቂት ተግ ብየ እንድጠይቅ ያነሳሳኝ ፤  “እራሱን እንዲከላከል ትዛዝ ሰጥተነዋል” ያሉት ሰራዊታቸው የሚያስተዳድራት “ነጻ ግዛት”  ከ7 ወራት በፊትም ስለመኖሯና ከነገር ስምነት የዘለለ  እውቅና እንደነበራት በገቡበት ጊዜና ከዚያም በኋላ በሰጧቸው መግለጫቸው አንዴም እንኳን ያላነሱበት ምኽኛት ነው። ቢያንስ ቢያንስ ያስመራው ድርድርም ከሷ በመለስ የተካሂያደ ስለመሆኑ በማናቸውም ወገን አመላካች ሀሳብ አለመቅረቡ ጉዳዩን ሾላ በድፍን ያደርገዋል። የሰነድና ማስረጃ  ጉዳይ ከተነሳ ስለግልጽነትና ተጠያቂነት የዶክተር አብይም መንግስት ለህዝቡ ከገባው ቃል አንጻር ያንበሳውን ድርሻ ሊወስድ ይገባዋል።

በደምሳሳው በይፋ ከሰማነው፤ ከተነገረንና በተነገረን ካወቅነው ፤  ነፍጥ አንግበው የኛ ያሉትን የህዝብ ወገን “ነፃ?” ሊያወጡ ጫካ የገቡ ወይም እንደዘንድሮ፤ ቀን እስኪያመች ባጎራባች አገሮች አድፍጠው የቆዩ ቡድኖች በሙሉ ፤ ወዳገር የተመለሱት “በሰላምና በሰላም ብቻ” የቆሙለትን ዓላማ ለማስፈጸም ቃላቸውን በመስጠት ነበር።  የኦቦ ዳውድም ኦነግ አገባብ ከሰሞኑ መግለጫው በፊት ከዚህ የተለየ አልነበረም።

ስለሆነም መግለጫው  ያረዳን ሀቅ “በእርቅና ሰላም ስም” ያለተጽኖ እንዲንቀሳቀስ እድል የተመቻቸለት የመሰለው ታጣቂ ቡድናቸው “በጉልበት ታብዮ”፤  “ሲፋጅ በማንኪያ፤ ሲቀዘቅዝ በእጅ” እንዲሉ የሚንቁትና ህጋዊነቱን ያልተቀበሉት መንግስት ፤ በሚያስተዳድራት አገርና ይሄው መንግስት በሰጣቸው ቢሮ ተቀምጠው ቀጭን ወታደራዊ መመሪያ እየሰጡ “በጠመንጃ አፈሙዝ አስገዳጅነት” ያሻቸውን ለማስፈጸም ልዩ መብት ያላቸው መሆኑን ለማሳየት የሄዱበት ርቀት ነው። መቼም እንዲህ ያለ ድፍረት በታሪክ ከተመዘገቡ ጥቂት ውነት መሳይ ቧልቶች መደዳ የሚዘነቅ ነው።

በመንደርደሪያዬ እንዳነሳሁት በይፋ የተረጋገጠ “ነፃ” የወጣ ግዛት ከሰባት ወራት በፊት መኖሩ ካልተረጋገጠ፤ አሁን የተነሳው ጥያቄ ለኦቦ ዳውድ ኦነግና ለመሰሎቻቸው በተራ ሽፍትነትና በነፃ አውጭ ሽምቅ ተዋጊነት መሀከል ያለውን ተራራ የሚያክል ልዩነት በቅጡ የገባቸው አለመሆኑን ወይም ሆን ብለውና አውቀው ፤ግርግር በመፍጠር ታግለው ያላስገኙትን ድል በጓሮ በር ገብተው ሊሞጨልፉ እየሞከሩ ሊሆን ስለሚችል ባይፈልጉትም አደብ እንዲቀሩ በትህትና ሊነገራቸው ይገባል።

ተራ ሽፍትነት ድንገቴ ነው፤ መነሻ ሰበቡ -ድንግቴ፤ አወጣጡ ድንገቴ፤ እድገቱም እንደውልደቱ ድንገቴ ነው። አስቀድሞ ያለጥናት፤ያለዝግጅት፤ በሆነ ሰበብ መሰስ ብሎ ፤ዱር ቤቴ ይልና ቀን-ቀን ከዋሻ ፤ ማታ-ማታ ጨለማን ተገን አርጎ ይዘርፋል፤ ሰላማዊ ኗሪን ያውካል፤ ወዳጅ ዘመዱን ሳይቀር እያሳቀቀና እያመሰ ፤ ውሎ አድሮ ሃይ ባይ ካጣ በዝርፊያው ይደራጅና ይገነግናል፤ አልፎ ተርፎም አውራ ነኝ ይላል፤ በሚንቀሳቀስበት አካባቢ ባለው ህዝብና ሀብት ላይም ይሰለጥናል።

አስቀድሞ በሃገር በወገን ላይ በደል ደርሷል ያለ ሸማቂ ቡድን ግን መነሻው ምንም ይሁን ምንም ፤ ከተራ ሽፍታ የተለየ ባህሪ አለው፤ ምክንያቴ ብሎ ለተነሳበት ዓላማ የሚሞትለትንና የሚገድለውን ወገን ለይቶ ፤ የሚጠላውን እያገለለ ፤የሚወደውን እያስከተለ ይደራጃል፤ አልሞና አቅዶ ይንቀሳቀሳል፤ አልሞና አቅዶ ጠላቴ ብሎ በፈረጀው ላይ ጥቃት እያደረሰ ፤ ወገኔ ያለውን እያበራከተ፤ ቆሜለታለሁ ያለው ዓላማ ግቡን እስኪመታ እያደራጀ፤ እያነቃና እያስተባበረ ወደህልሙ ይጓዛል እንጅ ተመቸኝ ብሎ ያስጠጋውን ህዝብ አይዘርፍም፤አይቀጥፍም።

ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ትግል ውስጥ የተሳተፍን፤ አብዛኞቻችን ተምረንና ተመራምረን ሳይሆን በልጅነት አዕምሮአችን በሰማነው ፤ በተወራልንና በተተረከልን ተደፋፍረን እየዘመርን የገባንበት “የፋኖ ተሰማራ፤ ነፃ አውጭነት” ትግል ፤ በሞዴልነት የመረጠው ጣሊያንን ድል የነሱትን የኢትዮጵያን ሽምቅ ተዋጊ አርበኞችን ስልት ሳይሆን  የኮሙኒስት አርበኞች የነበሩትን የቬትናሙን ሆቺሚኒንና የቦሊቪያውን ቼጉቬራን ሲሆን የተከተለውም የትግል ስልትና መርህ የቻይናው ማኦ ሴቱንግ ሽምቅ ውጊያ ስልት (Gorela Movement tactic & Strategy) እንደነበር አይዘነጋም።

ከ1960ዎቹ መጀመርያ አንስቶ በአፍሪካ የተካሂያዱ ፀረ-ቅኝ ግዛትና ፀረ ብሄራዊ ጭቆና ወይም ፀረ-ብዝበዛ ስርዐት ተቃውሞ ትግሎች አብዛኞቹ፤ አፍነውናል! ካሏቸው ስርዐተ-መንግስታት ለመላቀቅ ያካሂያዱት የሽምቅ ውጊያ ትግል ስልት ባመዛኙ ተመሳሳይነት ይታይበታል። በኢትዮጵያም ውስጥ ተፈልፍለው በሽምቅ ውጊያ “ነፃ” ለማውጣት ከተደራጁት አንጋፋ ድርጅቶች አንዱ ከነበረው ኦነግ ሽርፍራፊዎች መሃል የኦቦ ዳውድ ኦነግ አንደኛው ነው ።  የዚህ ድርጅት ፖለቲካዊና ታሪካዊ መነሻ ትርክት ምንም ይሁን ምን የተከተለውና ሲከተለው የነበረው  የነፃ አውጭነት ሽምቅ ውጊያ አደረጃጀት ባብዝሃኛው ከሌሎች በ60ዎቹ ከተነሱት “ነፃ አውጭዎች” የተቀዳ ስለመሆኑ ከስያሜ እስከ ዝርዝር አደረጃጀት ባህሪዎቹ ማስረጃ ማጣቀስ ይቻላል። በዚህ መነሻነት የኦቦ ዳውድን “ነፃ-ግዛት” ወግና “ሰራዊት” ከማኦ ሽምቅ ውጊያ ጽንሰ-ሀሳብ አኳያ እያነጣጠሩ መቃኘቱ በመጠኑም ቢሆን ከተጥረበረበ ጭጋግ አዘል እይታ ይታደገናል የሚል እምነት አለኝ።

ባጭሩ የማኦ ሽምቅ ውጊያ ትግል ስልት፤ መደራጀት(Organization) ፤ መጠናከርና(Consolidation) መቆጣጠር(Preservation) በሚባሉ ሶስት መስረታዊ ደረጃዎች የተከፈሉ ስልቶችን ይከተላል።ብርጋዴር ጌኔራል ሳሙኤል ቢ.ግሪፍ የተባሉ የዩኤስ አሜሪካ ማሪን ጦር አባል የነበሩ( Mao Tsetung on Guerrilla Warfare) በሚል ርዕስ ባዘጋጁት ጥናታዊ ጽሁፍ እንደሚያብራሩት ፤ በመጀመሪያው የመደራጀት (Organization) ዘመን የሽምቅ ውጊያውን የመረጠው ቡድን እጅግ ምስጢራዊና ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላ ስልት ራሱን “ጠላት” ከሚለው እይታ ደብቆ የትግል እንቅስቃሴውን ለማካሄድ በመረጣቸው ጫካና ተራራዎች እየተሹለከለከ፤ ያደረበትና የዋለበት እንዳይታወቅ ኮቴውን እያጠፋ፤ ከቋጥኝ-ቋጥኝ እየዘለለ ዱካውን አጥፍቶ ውስጥ ለውስጥ እራሱን እያዘጋጀ የሚቆይበት፤ ባብዛኛው ከተራ ሽፍትነት የዘለለ አቅም ያላበጀበት ጊዜ ነው። በእንዲህ ያለው ደረጃ ላይ ያለ ቡድን ከአሉ-አሉ ወሬ የዘለቀ “እከሌ የሚባል ቡድን” ወይም ጦር በእንዲሀ ያለ መንደር፤ በእንዲህ ያለ ዱር ውስጥ “ታይቷል አሉ” ከመባል ያለፈ ላቅመ -አስጊነት ያልደረሰበት ጊዜ ነው።

በሁለተኛው የመጠናከር (Consolidation) ወራት ደግሞ አልፎ-አልፎ ደፈጣ በማድረግ ከሚቀናቀነው የመንግስት ተቋም ላይ፤ ወይም ንክኪ ይኖረዋል ብሎ በጠረጠረው ወይም በፈረጀው ቡድን፤ ግለሰብ ተቋም፤ በመሳሰሉት ላይ የታቀደና የተጠና ጥቃት በማድረስ፤ ሥሥ ብልት እያየ በመኮርኮም፤ ያገኘውን ዘርፎና ነጣጥቆ ራሱን እያስታጠቀ፤ እንዲያም ሲል በደረሰበት መንደር ያገኘውን ኗሪ “መጣሁላችሁ፤ ለናንተ ብየ ነው፤ “ ምንትስዮ እያለ እየሰበከ፤ (የሚሰብክበት መንገድ እንደሚከተለው የፖለቲካ ዓላማ ላይ የተመሰረተ ቢሆንምና ቢለያይም) በመንግስት ላይ ቁሾ ያለውን የህዝብ ክፍል ማስተባበር የሚጀምርበት፤ ከዚህ የተነሳም ‘”እነ እከሌ እኮ “ የታችኛው መንደር ወይም ጎጥ ገብተው፤ ከፖሊስ ጣቢያ ሁለት ክላሽ፤ አንድ የቃታ ብረት እና 200 ጥይት ዘርፈው ተሰወሩ፤ በተኩስ ልውውጥ አንድ ፖሊስና ሶስት ሰላማዊ ሰዎች ጉዳት ደረሰባቸው….የመሳሰሉ ወሬዎች መናፈስ የሚጀምርበት ደረጃ ነው። ከዚህም ሲያልፍ እንደዘንድሮ ወሬ በሴኮንድ ዓለምን በሚያዳርስበት ዘመን፤ ምንጭ ሳይጠየቅ የሚቦጠርቁበት “ማህበራዊ “ የሚባል ሚዲያ በተስፋፋበት ጊዜ ፤ አራቱ ባራት መቶ ተባዝቶ፤ ተራ ዘረፋን “የጠላት የመጨቆኛ መገልገያ የነበረ ተቋም ላይ ባደርስነው ጥቃት አከርካሪውን ሰበርነው ፤ የሚሉ በጉራ የተባዘቱ ዜናዎች የሚነዙበት፤ ከወታደራዊው ድል ይልቅ ፖለቲካዊና የፕሮፓጋንዳ ድላቸው ሚዛን የሚደፋበት ፤ “በማኦኛ ቋንቋ” በጠላት ካምፕ ውስጥ ሽብር የሚለቅ የትግል ስልት የሚከተሉበት የትግል ደረጃ ነው።

ሶስተኛው አይነት ግና የሚፈጸመው ጥቃት ከመለስ-ቀለስ ደረጃ ይዝልና ጉልበትም፤ድርጅትም፤ተሰሚነትም ይጠናከርና በገቡበትና በደረሱበት ጎጥ ያለውን ጋራና ሸንተረር፤ ሸለቆና ቁጥቋጦ በመቆጣጠር ፤ በውስጡ ያለውን የመንግስት መዋቅርና ተቋማት በማፈራረስና በራስ አስተዳደር በመተካት፤ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ከአካባቢው የመንግስት እዝ ሰንሰለት በማለያየት በማኦ አደረጃጀት ደረጃ “ነፃ-ግዛት” እየተባለ የሚጠራውን የሚመሰርቱበት ደረጃ ነው። በዚህ ወቅት “ነፃ-አውጭ” የሚባለው ቡድን ከዚህ ነፃ ግዛቱ እየተንደረደረ አቅሙና ጉልበቱ እስከፈቀደለት ድረስ “የጠላት” በሚላቸው ጨርሰው  ከጠላት እጅ ያልወጡ ሌሎች የሀገሪቱን ከፍሎች በማጥቃት እየተስፋፋ፤እያደራጀ፤እያጠናከረና እየተቆጣጠረ የሚቅጥልበት ነው።

ለግንዛቤ እንዲረዳን ይህንን ካልኩ በሁዋላ የኦቦ ዳውድ ኦነግ የትኛው ደረጃ ላይ “ደርሻለሁ “ ወይም “ነበርኩ” እያለን እንደሆነ መግለጫውን መለስ ብሎ ማዳመጥ የግድ ይላል። መለስ ብየ የተባለውንና የሆነውን ሁሉ ሳጣጥመው ታዲያ፤ መንግስት ደጋግሞ እንደነገረንና ኦቦ ዳውድም አዲስ አበባ ሲገቡ በስታዲዮም ለታደለው ህዝብና በድፍን ዓለም ዙሪያ በቴሌቪዥን መስኮት ለሚከታተላቸው ኢትዮጵያዊ ባስተላለፉት ቃል ውስጥ “ነፃ ያወጡት ግዛት” እንዳላቸውና በዚያም ላይ የሰፈረውን ህዝብ ሲያስተዳድሩ መቆየታቸውን በገደምዳሜ እንኳን የሚገልጽ አንዳች አመላካች ቃል አላዳመጥኩም። ከዚያ ይልቅ ”የትጥቅ ትግሉን ሙሉ በሙሉ አቁመው በሰላምና በዲሞክራሲያዊ መንገድ በሚካሄድ ነፃ ምርጫ” ህዝብ የሚሰጣቸውን ብይን ለመቀበል መግባታቸውን አረጋግጠውልናል። ከዚህ በኋላም የድርጅታቸውን ወታደራዊ ክንፍ መፃኤ እድልን በሚመለከት ከመንግስት ጋር ስምምነት ላይ እንደደረሱም አስረግጠው ነግረውን ባጁ። የሰሞኑ መግለጫቸው ግን ከ6 ወራት በፊት ከነገሩን በመቶ ሰማንያ ድግሪ ሲቀይረው የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለማንሳት ተገደድኩ።

ጥያቄ አንድ፡ለኦቦ ዳውድና ግብረ አበሮቻቸው

ራሱን እንዲከላከል ትዕዛዝ አስተላለፍኩለት የሚሉት ጦራቸው የተቆጣጠራትን “ነፃ ግዛት” የያዘው ከሰባት ወር በፊት ወይስ ከስደት መልስ? እንዲያ ካልሆነ “በቁጥጥራችን ስር የምትገኘው” ያሏትን ግዛት የረፈደ ቢሆንም እንኳ ከስደት ይዘዋት ተመልሰው እንደሆን ማብራሪያ ብጤ ጨመር ቢያደርጉልን?

ጥያቄ ሁለት፡ ለኦቦ ለማ ወገን፤

እውን ከዳውድ ኢብሳ ጋር ድርድር ስትቀመጡ እናንተ ሳታውቁት ወይም የቀድሞዎቹ ኢህአዴጎች ከናንተ ደብቀው ለኦቦ ዳውድ ኢብሳ ባደራ የሰጧቸው ፤ ወይም በሙስና ያቀበሏቸው “በነፃ ግዛትነት” የተሰጠ መሬት በእጃቸው እንደሚገኝና እሱን በማደሪያነት ያለውድድር እንደምታጸኑላቸው  ቃል ተገባብታችሁ ከሆነ ግልጽ ብታደርጉልን፤ እኛም “ ነፍጥ ያነገቡ ቡድኖች በነፃ አውጭነት ስም ሰራዊታቸውን አዝምተው ከፌደራሉ መንግስት ነጥለው እንዳሻቸው በሚያስተዳድሯቸው ትትንሽ ግዛቶች እንዲኖር የሚፈረድበት፤በ21ኛው ክፍለ ዘመን የነፍጥ አንጋቢዎች ባሪያ እንዲሆን የሚፈረድበት ህዝብ እንዳለ ተቀብለን እርማችንን እንድናወጣ እድል ስጡን፤”

ጥያቄ ሶስት፡ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና በወሬ ትንፋሻችንን ሲያሳጥሩን ለከረሙ የማህበራዊ ገጽ  መረጃ ምንጮቻችን ፤ የጋዜጣና የቲቪ ወሬ አቀባዮቻችን፡፤

ባለፉት ሀያሰባት አመታት ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ፤ ከምዕራብ እስከምስራቅ ፤ መንግስትን በነፍጥ ለመጣል የተሰለፈ ቡድን ፤ አሳቻ ቦታ እየመረጠ አደጋ ከመጣል ያለፈ ተጠናክሮና ተደራጅቶ የመንግስትን መዋቅር ያነኳኮተ ፤ አይደለም ለወራት ፤ ለቀናት እንኳ የተቆጣጠራት “ስንዝር ነፃ መሬት” ካለች እናውቃለን በሉን። እንዲያ ካልሆነ የኦቦ ዳውድ “ሰራዊት” ተቆጣጥሬዋለሁ የሚለውን ግዛት በእጁ ያስገባው ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ ነው ለማለት ብንደፍር ነውር የለውም። ይሄ ደግሞ ትክክል ከሆነ የቻይናውን አብዮት መርቶ ባሸናፊነት ከተውጣው የቀዩ ጦር በኋላ ያለመራራ ትግል  “ በሰላምና በሰላም ብቻ ልታገል ቃል እገባለሁ” በሚሉት ዘመን አመጣሽ “የውጊያ ስልት” እስካፍንጫው የታጠቀን የመንግስት ሀይል አሞኝቶ አንዲት ጥይት ሳያጮህ፤ አንድ ሰው ሳይወድቅበት “እንደትሮይ ፈረስ” ተመሳስሎ ገብቶ ፤መሀል ከተማ ላይ መንግስት በሰጠው ቢሮ ላይ ተቀምጦ “የወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያውን የተከለ”፤ “የነፃ ግዛት ባለቤት “ ለመሆን የቻለ፤ በመንግስት ጦር ላይ ሰራዊቱ እርምጃ እንዲወስድ ትዛዝ መስጠቱን በኩራት መግለጫ እየሰጠ የቀጠለ ብቸኛ የ21ኛው ክ/ዘመን “ነፃ አውጭ” ድርጅት ያደርገዋል ማለት ነው። መልስ እንጠብቅ…???!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here