የኦሞ ኩራዝ 3 ስኳር ፋብሪካ መመረቁ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት እንደምንጨርስ ማሳያ ነው- ዶክተር አብይ አህመድ

0
58

አዲስ አበባ  ጥቅምት 4/2011 የኦሞ ኩራዝ 3 ስኳር ፋብሪካ መመረቁ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት መጨረስ እንደምንችል ማሳያ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

የኦሞ ኩራዝ 3 ስኳር ፋብሪካ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ እንዲሁም ሌሎች የሁለቱ አገሮች ባለስልጣናት በተገኙበት ዛሬ ተመርቋል።

ፋብሪካው ከቻይና ልማት ባንክ ከተገኘው 8 ቢሊዮን ብር በቻይናው ኮምፕላስት ድርጅት የተገነባ ሲሆን በቀን ከ8 እስከ 10 ሺህ ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም አለው።

በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ ዶክተር አብይ አህመድ ባደረጉት ንግግር ባለፉት ስድስት ወራት የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ አቅጣጫዎችን አስቀምጠን ትልቅ አቅም ያላቸው ድርጅቶችን በመምረጥ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

የዚህ ፋብሪካ መመረቅም “የተጀመሩ ፕሮጀከቶችን በፍጥነት መጨረስ እንደምንችል ማሳያ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ከዚህ በፊትም ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተጀምረው እንዴት ማለቅ እንዳለባቸው የተሳሳተ መንገድ ተከትለን ሳነጠናቅቃቸው ቆይተናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይም በሁሉም አካላት ትብብር ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለመጨረስ እንሰራለን ብለዋል።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በምረቃው ስነ ስርአት ላይ መገኘታቸውም “ሁለቱ አገሮች በጋራ ለልማት እንደሚሰለፉ ማሳያ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

በቀጣይም ለኢትዮጵያና ኤርትራ ብቻ ሳይሆን “ለመላው አፍሪካ የሚተርፉ ፕሮጀክቶችን በጋራ እንሰራለን” ሲሉም አረጋግጠዋለ።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው ዛሬ የተመረቀው ፋብሪካ “ኤርትራ ምን መስራት እንዳለባትና ምን ማሳካት እንዳለባት የሚያስተምር ነው” ብለዋል።

በዚህ ፋብሪካ ግንባታ የተሳተፉ ባለሙያዎችም ምን ያክል የመስራት አቅም እንዳለን ማሳያ ነውም  ብለዋል፡፡

የሁለቱን  አገራት ህዝቦችን  ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን በጋራ እንሰራለን ብለዋል ፕሬዝዳንቱ ።

በቀጣይም ቀጠናዊ ልማት በሚያመጡ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል ፕሬዝዳንት ኢሳያስ።

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ እንዳወቅ ሃብቴ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት  አመታዊ  የአገሪቷ  የስኳር ፍላጎት 700 ሺህ ቶን ደርሷል።

 ከዚህ ውስጥ አሁን ላይ በአገር ውስጥ የሚመረተው 50 በመቶው ብቻ መሆኑን በመግለጽ የእነዚህ አዳዲስ ስኳር ፋብሪካዎች መመረቅ ምርቱን ከ50 በመቶ በላይ እንደሚያደርሰው ነው የተናገሩት።

በስኳር ኮርፖሬሽን ውስጥ እስካሁን ለ65 ሺህ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ሲሆን ከዚህ ውስጥ ለ14 ሺህ 500 ሰው የስራ እድል የተፈጠረው በኦሞ ስኳር ፕሮጀክት መሆኑንም ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

በኦሞ ወንዝ አካባቢ እስካሁን አራት ፕሮጀክቶች ለመገንባት የታቀደ ሲሆን በዚህም  ለማህበረሰቡ ከስራ እድል ፈጠራ በተጨማሪ ለጤና ኬላ፤ ትምህርት ቤት፤ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፤ የመስኖና  የመንገድ መሰረተ ልማቶች እንዲስፋፋ አግዟል ሲሉም ጨምረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የስኳር ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ በ2003 ዓ.ም የስኳር ኮርፖሬሽን በማቋቋም እየሰራ ሲሆን በአገሪቷ የመጀመሪያው ስኳር ፋብሪካ ከ65 ዓመት በፊት የተቋቋመው ወንጂ ስኳር ፋብሪካ ነው።

ይህ ፋብሪካ በቀን 1ሺህ 400 ኩንታል የማምረት አቅም ነበረው።

Source ENA

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here