የመኪናዬ ታርጋ ሽፋን ላይ መልዕከቱ ደስ ብሎኝ የለጠፍኩት ጽሁፍ አለ፥ ምን ይላል፥ “What drives you?”

0
255

ከፋሲካ ገብርዬ

Ethiopians streets rally.

ሰላም ለሁላችሁ፥

የመኪናዬ ታርጋ ሽፋን ላይ መልዕከቱ ደስ ብሎኝ የለጠፍኩት ጽሁፍ አለ፥ ምን ይላል፥ “What drives you?”
ይህን ጥያቄ ዛሬ ለእናንተ እወረውረዋለሁ።

የኢትዮጵያ ጉዳይ እንቅልፍ ለስንት አመታት እንደነሳን መቁጠሩ ዋጋ ስለሌለው እንተወውና፥ እኔ ግን ሰሞኑን በበለጠ እረፍት ነስቶኛል። በየዕለቱ የምናየውና የምንሰማው ግጭት፣ ጠብ ያለሽ በዳቦ ዓይነት እሰጥ አገባና ያንን ተከትሎ ከየጎራው የሚሰነዘሩ የስድብ ዓይነቶች፣ ታላቅ ታናሽ የማይባልበት እርግጫ፣ ከተሜ ሰገጤ እየተባባሉ ያለው መናናቅ፣ አንዱ ብሄር የሌላውን ብሄር የሚገልጽባቸው ዘግናኝ ቃላት ወዘተ… በእውነት የአንድ አገር ልጆች ነን ወይ ያስብላል።

በፊት ለፌስ ቡክ ተሳዳቢዎች የተሰጠው ምክንያት ተከፋዮች እንደሆኑ እና የወያኔ የማጋጨት ደባ እንደሆነ ነበር። አሁን ግን እኔ እንኳን በአካል የማውቃቸው ግለሰቦች ስብዕናቸውን የማይመጥን ወገንተኝነትንና ስድብን ስራዬ ብለው ይዘውት ሳይ፥ በጣም አፈርኩ፥ አዘንኩ። ልጆቻችሁ የምትጽፉትን ቢያነቡ ወላጆቻችሁ ቢሰሙ ምን ይሏችሁ?

በአንድ ወቅት የከተማችን የማህበረሰብ ስብሰባ ላይ፣ ሰው ለሰው ክብር አጥቶ በሁለት ጎራ ተከፍሎ ሲተራመስ፥ አንድ ወንድም ያለውን መቼም አልረሳውም፥ “ስብሰባውን በአግባቡ ትመሩ እንደሁ ምሩት፥ አለዛ እዚህ ሰብስባችሁ አታባሉን” ነበር ያለው። ተደመሩ ተብሎ አገር ውስጥ የተሰበሰውን የፖለቲካ ማህበረሰብና ቀድሞ አገራችንን ጠቅልሎ ይገዛ የነበረውን ህወሀት መራሹን ስርዓትና በየክልሉ የተተከሉ ካድሬዎቹን እንዴት አስታርቆና አቻችሎ ለመሄድ እንደሚቻል ዕቅድ ካልነበረ፥ የቶሮንቶው ወንድም እንዳለው፥ ሰብስቦ ማባላት ነው የሚሆነው።

በሀምሌው የጠ/ሚ አብይ የሰሜን አሜሪካ ጉብኝት ወቅት፥ ቪዥን ኢትዮጵያ ባዘጋጀው ዝግጅት ላይ ስንገኝ፥ የሁለት-ሁለት ደቂቃ የጥያቄ ዕድል ለጠያቂዎች እንደሚሰጥ ስልተነገረን እኔ ጥያቄዎቼንና አስተያየቶቼን ጽፌ በ2 ደቂቃ ለክቼው በወረቀት ይዤው ነበር። ኋላም ጊዜ አጠረ ተብሎ ለጥያቄም ዕድል ሳይሰጥ ሊወጡ ሲሉ፥ ወረቀቴን ለባለመነጽሩ ጠባቂያቸው ሰጥቼው ነበር። እዛም ላይ ከዘረዘርኳቸው ጉዳዮች መሃል፥ ለምስራቅ አፍሪካ አካባቢያዊ (regional) ሰላምን የማምጣት የፖለቲካ ስትራቴጂያቸው የሚመሰገን ሲሆን፣ አገር ውስጥ ያለው ችግር ግን በዚህ ወያኔን አጋር የማሳጣት ከበባ ሊፈታ እንደማይችል እና፥ ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው ህዝብ ከህዝብ ጋር በግልጽ አሉኝ የሚላቸውን ታሪካዊ ቁርሾዎች ተነጋግሮ እንዲፈታ ዕድል ማመቻቸት እንደሆነ ከልቤ የሚሰማኝን ሃሳብ አስፍሬ ነበር።

ኢትዮጵያን ብለን እንጂ ከማናውቀውም ከምናውቀውም ግለሰብ ጋር በኢንተርኔትም በአደባባይም የምንመክረው፥ አለዛማ ቤታችን ችሎን እንኖር ነበር። ታዲያ ከምንናገረውና ከምናደርገው ድርጊት ጀርባ ምን “drive” እንደሚያደርገን ሁሌም መመርመር አለብን። ከድርጊታችን በስተጀርባ ፍቅር ከሌለና ለመልካም ብለን ካልሆነ ባንናገረው፥ ባንጽፈውስ ቢቀር። ለእኛም ለወገንም፣ ለአገርም ካልበጀ ዝምታ እኮ ወርቅ ነው።

ጅምሩ አበረታች ይመስል የነበረው የጠ/ሚ አብይ “የመደመር” አካሄድ ከቃላትና ከጊዜያዊ የፖለቲካ ስትራቴጂ አልፎ በተጀመረው መንፈስ ፍቅርንና ይቅርታን የሚዘራ ሆኖ አላገኘሁትም። ወያኔ የጀመረውን የክልል መንግስትነት የበለጠ አጠናክሮ፣ ዓርማና የድርጅት ስም ቀይሮ እንዳውም በግልጽ በሚታይ ሁኔታ በአገር ውስጥ፥ ትንንሽ አገሮች እየተፈጠሩ እንደሆነ ነው የታዘብኩት። የማዕከላዊ መንግስትን ተቀባይነት/legitimacy ለማሳጣት፥ ወያኔ በየጥጋጥጉ የቀበራቸውን የጸብ ፈንጂዎች እያፈነዳ ነው። የአገር ውስጥ ሚዲያዎችም የተቃዋሚ ድርጅቶችን ውይይት ከማስተላለፍ ውጪ፥ ህዝብ ለህዝብ ሲወያይባቸው አላየንም። የሰላም እናት፣ ወጣት ወዘተ እያሉ በየክልሉ የሚያዞሯቸው ግለሰቦችም ሆኑ የሰላም መድረክ እየተባሉ የሚዘጋጁ መድረኮች፣ ኢህአዲግ ለኢህአዲግ የፖለቲካ ድራማ የሚሰራባቸው መድረኮች ናቸው።

እውነተኛ ጥይቄዎች ይጠየቁ እስኪ፥

አንድ ጊዜ አማራ አንዴ አበሻ እያሉ የደቡብ ልሂቃን ከሚሽነሪዎች የተሞሉትን ትርክት ይዘው በደለን ያሉት ህዝብ፣ መቼና እንዴት እንደሆነ በአደባባይ ቀርበው በማስረጃ ያስረዱ።

ትግራይ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ተለይቶ በማዕከላዊ መንግስት የደረሰበት በደል ካለ፥ ይህንን ህዝብ ለህዝብ ተቀራርቦ ምን እንደተፈጠረ ፊት ለፊት ያስረዱ።

የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ፖርቱጋሎች፣ ጣሊያኖች፣ ስዊዲሾች ወዘተ ለማዳከም ቱርኮችና ደርቡሾች ለማጥፋት ሞክረው ያልተሳካላቸውን በአገር በቀል ወኪሎች ለመከፋፈልና ለማጥፋት የተሞከረውና ተከባብሮ እንደእየእምነቱ መኖር ያልተቻለበትን ምክንያት አውቃለሁ የሚሉ ያስረዱ።

አንዱ መጤ አንዱ ነዋሪ እየተባለ ሰው ለሰው የሚጋደልበትን ምክንያት፥ ከአፈር እንደተክል የበቀሉ ዜጎች ካሉ እስኪ ቀርበው ያስረዱ።

ከተማ በመወለዳቸውና ዘመናዊ ትምህርት በመማራቸው ብቻ የቀደምቶቻችንን ማንነት ባላገር፣ ሰገጤ፣ መሀይም እያሉ የሚያናንቁ፥ እስኪ ቀርበው የእነሱ “ስልጣኔ” ምን እንደፈየደ ያስረዱ።

ራሱን የናቀ፣ ማንነቱን የካደ፣ መነሻውን የረሳ፣ በአይኑ ያለውን ጉድፍ የማያይ፣ ጥላቻን የተሞላ እንዲህ እንደዘመናችን አይነት ትውልድ አገራችን አፍርታ የምታውቅ አይመስለኝም።
ፖለቲካውን ተዉት፥ ለመጠፋፋት ምን ፖለቲካ ያስፈልጋል? ደም መጠማት ብቻ በቂ ነው። እንደሰው እናስብና ራሳችንን እንመርምር።

ቅኝ አልተገዛንም ብለን የፎከርነው ሰዎች ቅኝ ከተገዙት ባልተናነሰ፥ ምናልባትም በባሰ ሁኔታ ራሳችንን መሆን አቅቶናል፣ ለከፋፍለህ ግዛው እጅ ሰጥተናል፣ የነገን ማየት ተስኖናል። እኔ መጸለይም አቅቶኛል። ግን ይሄን እላለሁ፥ ዜግነቴም ማንነቴም የእግዜር ፍጡር የሰው ልጅ ነኝ። ፈጣሪ ሆይ፥ ከወገኖቻችን ጋር ተሳስበን የምንኖርበትን ጥበብ ስጠን። ማንም ማንንም በክፋት አጥፍቶ መንገስ አይችልም። ለመበጥበጥ ከሆነ አንድ በሬ እንኳ በረትን ያውካል። ይሄ ብሄር ቁጥሩ ትንሽ ነው፣ መሬቱ ደረቅ ነው ለምለም ነው፣ ይሄ ግለሰብ ሀብታም ነው፣ ምሁር ነው ወዘተ እያልን ስንናናቅ ተያይዘን እንዳንጠፋ። ሁላችንም ለሁላችንም እናስፈልጋለን።

ከቅርብም ከሩቅም ታሪካችን መማር ያልቻልነው ነገር ቢኖር፥ ጥያቂዎች ሲታፈኑ የሚጠፉ ይመስለናል። ያልተነፈሰ፣ በግልጽ ያልተነገረ ነገር ስር ሰዶ ያጠፋናል።

ጠ/ሚ አብይ ስልጣን ሲረከቡ እንዳደረጉት በግልጽነት ችግሮችን በአደባባይ ከህዝብ እየተማከሩ ይፍቱት። እውነቱን ያወቀ ህዝብ ያዝናል፣ ከጎንዎም ይቆማል። የአገራችንን የተወሳሰቡ የፖለቲካና ማህበራዊ ችግሮች በሴራና በስሌት ሳይሆን እንደጀመሩት በፍቅርና በይቅርታ መንፈስ ለመፍታት ይሞክሩ። ህዝብ የደገፎት ለእዛ ነው። እንደአንድ ኢትዮጵያዊት ሴት የሚሰማኝን ተናግርያለሁ። የጀመርነው አካሄድ የትም አያደርስም። የዜሮ ድምር ፖለቲካ ማለት ይሄ ነው።

እንደዜጋ አንድ ሆነን ቆመን፣ ካጠፋን ተማምነን ይቅር ተባብለን ድንበራችንን እንጠብቅ። በየድንበሩ ላይ ሰውም ቤትም እየተቃጠለ፥ መሃል ከተማ ላይ ነጭ በነጭ የሆነ ቢሮ ውስጥ እየተሸነጋገሉ የሚፈታ ችግር የለም። መንግስትም ተቃዋሚዎችም፥ ምርጫ ወዘተ ከሚለው ውይይታችሁ ባልተናነሰ ለህዝብ የሰላምና የይቅርታ ጥሪ አድርጉ፣ ያስቀየማችሁትን ይቅር በሉኝ በሉ። ለፍቅርና ለመልካም ነገር ሲባል ዝቅ ማለት፥ ትልቅነትን ነው የሚያሳየው። ዓለማችንን ፈጥሮ እንድንኖርበት አምላክ ሲሰጠን፥ በሃላፊነት እንድንመራው ነው። የተበተነውን ሰብስቡ! በየስፍራው የሚሰቃዩ፣ የሚሰደዱ፣ የሚሞቱት ልጆቻችን ቢሆኑስ ብላችሁ አስቡ። ወገን አንድ ጥግ እያለቀሰ እኛ ሰላም ልንሆን አንችልም። ይኸው ባህር ተሻግረን ያለነውን እንኳን እንቅልፍ ነስቶናል።

©ፋሲካ ገብርዬ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here