ከኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ

0
36

ከኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ
********************************************

ለውጡን ከሚያደናቅፉ እና ሂደቱንም ከሚያውኩ ተግባራት መከላከል የኢትዮጵያውያን ሁሉ የጋራ ኃላፊነት ነው!

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የዘንድሮን የዘመን መለወጫ በዓል ያከበሩት ከቤተሰባቸው ተለይተው በሞቃታማው የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ላይ ነበር። መላው ኢትዮጵያውያንም አዲሱን ዓመት የተቀበልነው “በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር” በሚል እሳቤ ለበርካታ አሥርት ዓመታት ያህል ከአገርና ከወገን ርቀው የኖሩ ወገኖቻችንን በማሰባሰብ እና ጠንካራ ትስስር ካለን የኤርትራ ህዝቦች ጋርም በመደመር መንፈስ ነበር።

የኢትዮጵያውያን አንድነት እና ፍቅር ጉልበቱ እስከምን ድረስ ሊሄድ እንደሚችል በሚያረጋግጥልን መልኩ ሁሉም የአጎራባቾቻችን አገራት መሪዎች ፍጹም ባልተለመደ አኳኋን ለኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በዋዜማው ወቅት አስተላልፈዋል። ይህም አገራችን የተያያዘችው የለውጥ እንቅስቃሴ በድንበር ያልታጠረ፣ ሁሉንም የአካባቢውን አገሮች ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን በተግባር ከማረጋገጥ እና በቀጣይም ከአገራችን ኢትዮጵያ ጋር መወዳጀት የሚያስገኘውን ፋይዳ በጥብቅ ከመገንዘብ የመጣ መሆኑን በጥብቅ መረዳት ያሻል።

በአፍሪካ ቀንድ የምናራምደው አቋም የኢትዮጵያን የአስታራቂነት ሚና እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት በእጅጉ አሳድጎታል። በተመሳሳይ በአገር ውስጥ እውነተኛ ሰላምን፣ ፍትህን፣ እኩልነትን እና ነጻነትን ለማስፈን ሲባል በመንግሥት የተወሰዱት ታላላቅና ተጨባጭ እርምጃዎች የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ቀልብ የገዙ፣ እውቅና እና ድጋፍ ያስገኙ ናቸው።

ህዝባችንም ለማህበረሰባዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ዝግጁነቱን በሚያረጋግጥ መልኩ በዘመን መለወጫ በዓሉና በዋዜማው ወቅት በበጎ ተግባራት ላይ ተሰማርቶ አኩሪ ተግባራትን ፈጽሟል። ከከተሜነት መስፋፋት ጋር ተያይዞ እያደገ የመጣውን የግለኝነት አስተሳሰብ የመላበስ እና በአንጻሩ እየተሸረሸሩ ያሉትን የመተሳሰብና የመደጋገፍ ኢትዮጵያዊ እሴቶች በፍጥነት የመመለስ ብርቱ ፍላጎት በሚያንጸባርቅ መልኩ ለአብነትም የበርካታ አቅመ ደካሞች የተሰበረ መንፈስ መጠገን፣ ቤቶቻቸውን መጠገን እንዲሁም በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ትምህርታቸው ሊስተጓጎልባቸው የነበሩ ሕፃናትን የመታደግ ተግባር ተከናውኗል።

እነዚህን እና የመሳሰሉ ውብ እና ተስፋ ተስፋ ሰጪ ተግባራትን እያየን ባለንበት ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ አካባቢዎች አንዳንድ ወጣቶቻችን በፖለቲካ ድርጅቶች አርማና የባንዲራ ጉዳይ ንትርክ ሳቢያ ወደ ሁከት የመግባት ሁኔታ ተከስቷል።

የዚህ ሁከት ፍላጎት መነሻ በዋናነት በመንግስት አመራር፣ በሰፊው ህዝብ፣ በወጣቶች፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ባሉ የለውጥ ሃይሎች ርብርብ የመጣን አገራዊ ለውጥ ዓላማ በውል ካለመገንዘብ የመጣ ችግር ነው።

ይህ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ፊት አውራሪነት ተግባራዊ በመሆን ላይ ያለው አገራዊ ለውጥ ከባንዲራ ቀለማት በላይ ትላልቅ ዓላማዎችን አንግቦ የተነሳ ነው። የለውጡ ዓላማ እውነተኛ ፍትህን፣ እኩልነትን፣ ነጻነትንና ልማትን ማረጋገጥ ነው። ጉዳዩ ይህ ሆኖ ሳለ ገና ከወዲሁ በጥቃቅን ልዩነቶች ላይ ተመስርቶ የሚካሄድ አፍራሽ እንቅስቃሴ በምንም መልኩ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።

በባንዲራ ቀለምም ይሁን ከፖለቲካ ድርጅቶች አርማዎች በላይ ባሉ በርካታ ጉዳዮች ላይ ያሉ የአመለካከት እና የሃሳብ ልዩነቶች ሁሉ እንደ ፀጋ እና እንደበረከት ሊቆጠሩ ይገባቸዋል። ይህንን ዕውነታ ተቀብሎ ልዩነቶችን በሰለጠነ አካሄድ፣ በውይይት እና በሃሳብ ትግል ብቻ መፍታትን ከዚህ በኋላ ባህላችን ልናደርግ ይገባል።

ለእኛ ኢትዮጵያውያን የሚያዋጣንም መንገድ ይሄው ብቻ መሆኑን ከእኛ በላይ ሌላ መካሪ ሊኖረን አይችልም። ሩቅ እያሰብን ከወዲሁ በትናንሽ ጉዳዮች ተወለካክፈን የምንወድቅ ከሆነ ውጤቱ የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ የለውጥ ሂደት ማደናቀፍና ማጓተት አሊያም አገራችንን ለከፋ ችግር መዳረግ እንጂ ሌላ ፋይዳ ሊያስገኝልን አይችልም።

በመሆኑም የፖለቲካ ልሂቃን፣ የሲቪክ፣ የኃይማኖት እና የትምህርት ተቋማት እንዲሁም ወላጆችና የብዙሃን መገናኛ ሙያተኞች ወጣቶቻችንን በጠራ አመለካከት በማረምና በማነጽ ረገድ የሚጠበቅብንን ሚና መጫወት ያለብን በዚህ ወቅት ነው።

ወጣቶቻችንም በበኩላቸው እነሱን ጨምሮ በተካሄደ ተጋድሎ የተገኘውን ተስፋ ሰጪ ውጤት በፍጥነት ወደ ፊት ከመገስገስና ከተነሳበት ዓላማ እንዳይስት የበኩላቸውን ወሣኝ ሃላፊነት በመወጣት ለለውጡ ያላቸውን እውነተኛ አጋርነት በተግባር እንዲያረጋግጡ የኢፌዴሪ መንግሥት ጥሪ ያቀርባል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here