አዲስ ይፋ የሆነው የትምህርት ፍኖተ-ካርታ ትምህርት ሚኒስቴርን ሦስት ቦታ የሚያደራጅ ነው

0
68

ነሐሴ 16፣2010

አዲስ ይፋ የሆነው የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታ ትምህርት ሚኒስቴርን በሦስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የሚያደራጅ መሆኑ ተጠቆመ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተካሄደው ውይይት የቀረበው አጠቃላይ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ፣ የከፍተኛ ትምህርትና የትምህርት ዘርፍ አስተዳደር ላይ ማሻሻያ ቀርቧል።

በትምህርት ዘርፍ አስተዳደር ላይ ማሻሻያ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ጄይሉ ዑመር እንዳሉት ፍኖተ-ካርታው ብዙ መዋቅራዊ ለውጦችን የያዘ በመሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር በሦስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እንዲደራጅ የሚያደርግ ነው።

በአዲስ መልክ የሚቋቋሙት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ሚኒስቴር፣ አጠቃላይ የትምህርትና ስልጠና ሚኒስቴር እና የክህሎትና ሥራ ፈጠራ ሚኒስቴር ተብለው እንደሚዋቀሩ ገልጸዋል። ዶ/ር ጄይሉ እንዳሉት የተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ቆይታ ጊዜ ዝቅተኛው አራት ዓመት ሲሆን እንደ ምህንድስናና ህክምና የትምህርት ፕሮግራሞች ደግሞ ስድስት ዓመት እንዲሆኑ ሀሳብ ቀርቧል።

የትምህርት መስጫ ቋንቋዎችን በተመለከተም እስካሁን ኢትዮጵያ የቋንቋ ፖሊሲ የሌላት በመሆኑ በቀጣይ እንደ አስፈላጊነቱ ሦስት ቋንቋዎችን በአጠቃላይ ትምህርቱ ላይ ለመጠቀም መታቀዱን ጠቁመዋል። ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በከፍተኛ ትምህርት ማሻሻያ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ እንዳሉት ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ የሚከፈቱ ዩኒቨርሲቲዎች ያለ በቂ ሀብትና ቤተሙከራ ሊሆን አይገባም። በዝግጅት ላይ ያለው ፍኖተ-ካርታም እነዚህን ሃሳቦች የያዘ ሲሆን የትምህርት ፕሮግራሞች ሲከፈቱ በገለልተኛ አካል ታይተው ለኀብረተሰቡ ጥቅም የሚሰጡ መሆናቸው ሲረጋገጥ ብቻ ይከፈታሉ ብለዋል። ከፍኖተ-ካርታው አዘጋጆች መካከል ዶክተር መላኩ ዋቁማ እንዳሉት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ ተደራሽነት ፍትሃዊነት የጎደለው ስለሆነ ፍኖተ-ካርታው ይህን ችግር የሚፈታ መሆን አለበት።

በተለይም በገጠርና በከተማ፣ በአርብቶ አደርና በሌላው አካባቢ የሚስተዋለውን የፍትሃዊነትና የተደራሽነት ጥያቄ በሚፈታ መልኩ ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት።

ስልጠና በሚሰጥበት ወቅት ተጨባጭና ተግባራዊ በሆኑ ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ ሰልጣኞች ወደ ኀብረተሰቡ በሚቀላቀሉበት ወቅት አቅም የሚፈጥር ሊሆን ይገባል ብለዋል። ሌላው አዘጋጅ ዶክተር ፈቀደ ቱሊ በበኩላቸው የመምህራን ምልመላ በሚደረግበት ወቅት በአብዛኛው ጊዜ በከፍተኛ ውጤት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎችን ሲሆን ተመልማዮቹ ሙያውን እንደሚፈልጉ ቅድሚያ ማረጋገጥ ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል። የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታ ለቀጣዩ 15 ዓመት ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ሲሆን በተሳታፊዎቹ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ምንጭ፡‑ ኢዜአ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here