በክልሉ ጥፋት ለመፈጸም ጫካ ውስጥ ሲሰለጥኑ ከነበሩ ግለሰቦች መካከል 51 ተያዙ

0
343

አሶሳ ጥቅምት 4/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕዝብ ላይ ጥፋት ለመፈጸም ወታደራዊ ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ 51 ግለሰቦችን መያዙን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አስታወቁ።

ኮሚሽነር ሰይፈዲን ሃሩን ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ግለሰቦቹ የተያዙት ኅብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ የክልሉ ልዩ ኃይል ሰሞኑን በአሶሳ ዞን ባደረገው አሰሳ ነው፡፡

በአሰሳው በገንገን ቀበሌ ልዩ ስሙ ዛላን ወንዝ አካባቢ በህገ-ወጥ መንገድ ጫካ ውስጥ ገብተው ስልጠናውን ሲያካሄዱ የነበሩ 31 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ፣20ዎቹ ደግሞ እጃቸውን ሰጥተዋል፡፡

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ሰልጣኞች የ13 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ህጻናት ይገኙበታል ብለዋል።

በቦታው ተንቀሳቃሽ ስልኮች መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች፣ ፓስፖርቶች፣ የተለያዩ የመታወቂያ ካርዶች መገኘታቸውን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

ልዩ ኃይሉ ግለሰቦቹ ከሁለት ሄክታር በሚበልጥ መሬት የሰሩትን ካምፕ ሙሉ በሙሉ ማውደሙንም ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው ላይ ከነበረው ኃይል የተወሰነው ወደ አጎራባች አገር እንደሸሸም አስታውቀዋል፡፡

ግለሰቦቹ ራሱን የበርታ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (በህነን) ብሎ ከሚጠራው ኃይል ተለይተው የወጡ ቡድን አባላት ሊሆኑ እንደሚችሉ ኮሚሽነር ሰይፈዲን ጠቁመዋል፡፡

ግለሰቦቹ በሥፍራው ከአንድ ወር በላይ ስልጠና ሲከታተሉ እንደነበር አመልክተዋል።

”ግለሰቦቹ ይህን ያህል ጊዜ ስልጠና ሲወስዱ የጸጥታ ኃይሉ የት ነበር?” በሚል ከኢዜአ ሪፖርተር ለተነሳላቸው ጥያቄ  ኮሚሽነሩ፣ የክልሉ መንግሥት ትኩረት በአሶሳና አካባቢው የተከሰተውን የውስጥ የጸጥታ ችግር ማርገብ ላይ መጠመዱ እና አካባቢው መንገድ የሌለውና ጠረፋማ በመሆኑ ለጸረ-ሠላም ኃይሎቹ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ነው ”ብለዋል፡፡

ክልሉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ከአገር መከላከያ ሠራዊትና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ተቀናጅተው በመሥራት ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ሕዝብ በክልሉ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ድጋፉን እንዲያጠናክር ኮሚሽነር ሰይፈዲን ጠይቀዋል፡፡

source ENA

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here