ምሁራን ልዩነቶችን የማስተናገድ ባህል አላዳበርንም (ዶ/ር አክሎግ ቢራራ)

0
16

ዶክተር አክሎግ ቢራራ (የዓለም ባንክ አማካሪ የነበሩ ከአሜሪካ)

Author, Dr. Aklog Birara

አክሎግ ቢራራ (ዶ/ ር)

ይህ ምልልስ ከጋዜጠኛ እድክንድር ነጋ ጋር የተካሄደ ሲሆን፤ በውጭ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም እንዲያውቁት በሚል መንፈስ ትንተናየ በኢትዮጵያ ከወጣ በኋላ፤ በራሴ ውሳኔ ያቀረብኩት መሆኑን እገልጻለሁ፤ ጋዤጠኛ እስክንድር ላደረገልኝ ማስተካከያና ትብብር ምስጋናየን አቀርባለሁ፤ በአገር ቤት ሆኖ የሚሰጠውን አገልግሎት አደንቃለሁ።

ምሁራን እነማን ናቸው?

መጀመሪያ በትርጉም እንግባባ፡፡ ምሁራን ስንል ምን ማለታችን ነው? በአብዛኛው፣ ምሁራን ተብሎ የሚጠራው ክፍል ስለ አገሩ፣ ሕዝቡ፣ ህብረተሰቡ ማህበረሰባዊ፣ መንፈሳዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች አዕምሮውን፣ እውቀቱንና ችሎታውን በግልና በጋራ ተጠቅሞ ጥልቀት ያለው ጥናትና ምርምር በማድረግ መፍትሄዎችን ጸንሶና አዘጋጅቶ የሚያቀርብ ነው፡፡ ጥናቱና ምርምሩ የሚደረገው ለግል ጥቅም፣ ለዝና፣ ለንግድ፣ ለወገንተኝነት ወይም ለውጭ ኃይል ፍጆታ አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ ምሁራን የሚጫወቱት ሚና ለአገርና ለሕብረተሰብ ገንቢ እንደሆነ ግን ብዙዎችን ያግባባል፡፡

ምሁራን ወይንም ጠበብቶች፣ በተለያዩ ሀገራት የተለያዩ ደረጃዎች ይሰጧቸዋል፡፡ ለምሳሌ፣ የጃፓን ምሁራን ‹‹ታሪክ፣ የጥንት ባህል፣ ቅርሶች፣ ኃይማኖት፣ ልምዶች፣ ትምህርት፣ ቴክኖሎጅ፣ እድገት፣ ቤተሰብ ወዘተ. ተለያይተው አይታዩም፤ የተያያዙ ናቸው›› ይላሉ፡፡ ለዚህ ነው፤ ጃፓን በቴክኖሎጅ የረቀቀች ብትሆንም፣ ባህሏን ያስከበረች አገር ሆና የቆየችው፡፡ በጃፓን ምሁራን የሚከበሩት “ፈረንጅ” ስለሆኑ ሳይሆን፣ ጃፓናዊነታቸውንና፣ ከሌላው አገር ጋር ተወዳዳሪ የሆነ ከፍተኛ ትምህርት፣ ጥናት፣ ምርምር፣ ኢኮኖሚ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ወሳኝ መሆናቸውን ተቀብለው፣ ባህልን ማስከበርና ዘመናዊነትን አብረው ያስኬዷቸው፡፡ በዚህም፣ ምሁሮቻቸው ጃፓንን ጠንካራ ለማድረግ የሚያስችሉ ግብዓቶችን ሳይታክቱ ያቀርባሉ፡፡ ተቀዳሚ ኃላፊነታቸው ለጃፓንና ለሕዝባቸው ነው፡፡ ጃፓናዊነትና ጃፓን ለድርድር አይቀርቡም፡፡ ይህ አይነቱ የምሁራን ሚና እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና እና ቬትናም ባሉ ሀገራት ታይቷል፡፡ ሚናቸው የሚዳሰስና ለፍትህ፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለሰላም፣ ለእርጋታ፣ ለዘላቂ የሕዝብ እድገትን ማእከል ላደረገ ልማት ወሳኝ መሆኑ ተመስክሮላቸዋል፡፡

እኔ በተደጋጋሚ መነሻውን የማያውቅ ሕዝብ መድረሻውንም አያውቅም እያልኩ ስከራከር የቆየሁት ለዚህ ነው።

እኛ አገር ተከል ቴክኖሎጂን እንንቃለን

የኢትዮጵያ ተመራማሪዎች፣ በተለይ ምሁራን፣ አገር ተከል ሆነው በኢትዮጵያዊያን ተጸንሰው፣ ተሻሽለው፣ ለምርት ኃይሎች፣ ለማህበረሰቡ አገልግሎት፣ ለንግድና ሌላ ስራ ጠቃሚ የሆኑትን ባህሎችና ቅርሶች እውቅና ሰጥተው፤ተንከባክበው፣ አክብረው እንዲሻሻሉ አላደረጉም፡፡ለምሳሌ፣ የብረታ ብረት፣ የሸክላ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የመስኖና የከብት እርባታ ስራዎችን ሀገርኛ ይዘታቸውን ሳይለቁ እንዲሻሻሉ አልተደረጉም፡፡ ኢትዮጵያ የእርሻ ልምድ ካላቸው አገሮች መካከል አንዷ ብትሆንም፣ ይህን የኢኮኖሚ ክፍል በራሳችን ጥረትና ምርምር ለማሻሻል አልቻልንም፡፡ ላሊበላን የሰራ ሕዝብ፤ ዛሬ ተመጣጣኝ ሕንጻ ለመስራት አልቻለም። ‹‹እኛ ካላሻሻልነው ማን ሊያሻሽልልን ነው?›› ብለን ራሳችን ለመጠየቅም አልደፈርንም፡፡ አገር ተከል ቴክኖሎጂዎችን የናቅናቸው ይመስለኛል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ የሴቶች ልብስን ጌጥ አሳምሮ ልዩ ልዩ ጥበቦችን የሚያመርት አገር ያለ አይመስለኝም። ሴቶች በሙሉ እነዚህን መለያዎች አገር አቀፍ በሆነ ደረጃ የዘወትር ልብስ የማያደርጉበት ምክንያት ለኔ ግልጽ አይደለም። ወደ አርእስቴ ልመለስ!!

በነገራችን ላይ፤ እያንዳንዱ ግለሰብ በተወሰነ ደረጃ ምሁር ነው፡፡ ምሁር ከእናቱ፣ ከአባቱ፣ ከጓደኛውና ከሌላው አልተማረም፡፡ በተለምዶ ምሁር የምንለው የሚለየው፣ ለተሰማራበት ሙያ እንዲረዳውና እውቀቱ እንዲጨምር ከፍተኛ ትምህርት ማግኘቱ ነው፡፡ የመጣንበትን ሁኔታ ባንረሳ፣ ህብረተሰቡን በበለጠ ደረጃ በትህትና ለማገልገል እንችላለን፡፡ ሕብረተሰቡ ከእኛ በበለጠ ያለበትን ሁኔታ ያውቃል፤ ምሁራን ከሕዝብ ለመማር ብንችል፣ ከብዙ ስህተቶች ልንቆጠብ በቻልን ነበር፡፡ እርስ በርሳችን እንቻቻል፤ እንደማመጥ ነበር፡፡

ጃፓኖችና ከሕዝብ ይማራሉ፤ የጥንቱን ያሻሽላሉ እንጅ አይንቁም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ልዩነቶችን የማስተናገድና የማክበር ባህል ገና አላዳበርንም፡፡ ይህ ለአብሮነነትና ለዴሞክራሲትልቅ ማነቆ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ሲጠቀሙበት የቆዩት መርህና ስልት ብሄራዊ ተቋማትን አፈራርሶ የሌለ ልዩነትን ማጠናከር ነው።

ይህ ሁኔታ የሚያስታውሰኝ የደቡቡ አፍሪካው ታዛቢና ተቆርቋሪ አለን ፔይተን የዛሬ ሰባ ዓመት የጻፈውን የደቡብ አፍሪካን ልምድ፤ ባህል፤ ታሪክ፤ ኑሮ፤ አስተዳደርና ሌላ በአጠቃላይ አገር ተከል የሆኑ ተቋማትን መፈራረስ ነው። ጥቁር አፍሪካዊያን ታሪክ፤ ባህል፤ የአስተዳደር ልምድ እንደሌላቸው ያደረገውን የነጮች አፍራሽ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት ባህል ማለቴ ነው።  Cry, the Beloved Country በተባለው የማይረሳ መጽሃፉ አለን ፔይቶን እንዲህ ብሎ ነበር። “Cry for the broken tribe, for the law and custom that is gone…Cry, the beloved country, these things are not yet at and end.” His most poignant thesis was this. “The tragedy is not things are broken. The tragedy is that things are not mended again…..የሚያሳዝነውና የሚያስፈራው አገር ተከል ባህሎች፤ ተቋሞች፤ ልምዶች መፈራረሳቸው ብቻ አይደለም። አሳኙ ክስተት የፈረሱት ሊጠገኑና ሊመለሱ አለመቻላቸው ነው።”

ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ሆነ ተብሎ የተመሰረተው ጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ኢትዮጵያዊነት ባህልና ተቋማት በቀላሉ መልሶ ለመተካት አይቻልም። የምሁራን ተግዳሮት ከዚህ ላይ ነው። ሁሉም የሚያስበውና የሚታገለው ለራሱ ቡድን፤ ለራሱ ክልል፤ ለራሱ ዘውግ ከሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማን ሊታገል ነው።

የምሁራን ኃላፊነት ምንድነው?

ለማነጻጸር፣ የተማሩ (ስኮልራስ) ተብለው የሚታወቁት ግለሰቦች ጊዚያቸውን፣ ልምዳቸውንና ትምህርታቸውን የሚያጠፉት በዓለም ዙሪያ ሌሎች ያበረከቱትን ጥናት፣ ጽሁፍ፣ ትንተና፣ ሃሳብና ምርምር እየሰበሰቡ በማጤን፣ በመመራመር፣ በመፈተሽ፣ በመተርጎም፣ በመተንተን፣ በማዛመድ፣ በመሰላቸውና ተቀባይነት በሚኖረው መልክ በማሻሻል እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህም፣ የዓለም ሕዝብ ህይወት እንዲሻሻልና የጋራ ግንዛቤ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ስኮልራስ ራሳቸውን ለጥቅም ብለው አያበረክቱም፤ በሃሳባቸው አይነግዱም፡፡ የሌሎችን አስተዋጾ ያከብራሉ፡፡ የሚመሩበት መርህ አላቸው፡፡ ከመርሆዎቻቸው መካከል፡-

ምርምርና ቲኦሪ፣ ለምሳሌ፣ የሊበራል ዴሞክራሲው “የነጻ ገበያ ይሰራል” የሚለውን ማጠናከር፣ ለዚህ የሚረዱ ልዩ ልዩ ጥናቶችን መሰብሰብ፤

በግልም ሆነ በመንግሥት ስራ የሚገኝ እውነተኛ የስራ ልምድና እውቀትን አግባብ ባለው መንገድ መጠቀምና፤

የግል እሴቶች፣ ለምሳሌ ሃቀኛነት፣ ፍትህ፣ የሕግ የበላይነት ወሳኝ ሚና ስላላቸው፣ እሴቶቹ በጥናትና ምርምር፣ በጽሁፍ ማንጸባረቅ፡፡

ምሁራንና ‹‹ስኮልራስ›› የተለያዩ ስለሆኑ የአንድ ሳንቲም ግልባጭ አድርገን እንዳንጠቀምባቸው አሳስባለሁ፡፡ በማንኛውም አገር፣ ምሁራን ገንቢ ስራ ለመስራት የሚችሉበት እድል አላቸው፡፡ ሆኖም፣ ይህን እድል የሚጠቀሙት የተወሰኑ ናቸው፡፡ አንዱ ችግር በዘውግና በኃይማኖት ያለው ልዩነትና መበታተን ነው፡፡ ሌላው፣ በጉራና በትእቢት መበከላቸውና “እኔ ብቻ አውቃለሁ” የሚል እውቀት ያልፈታው ብሂል መከተላቸው ነው፡፡ የማንንም አገር ባህል ተውሰው በአገራቸው ሕዝብ ላይ ጫና ማድረጋቸውም ሌላው ነጥብ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ “የብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝቦች ጥያቄ” ነግሶ የቆየውና አሁንም ገና መፍትሄ ያላገኘው በዚህ የተነሳ ነው፡፡ ራስችን የፈጠርነውን ችግር በጋራ ሆነን፣ በድፍረትና ቆራጥነት እንዴት መፍትሄዎች ወይንም አማራጮች ማቅረብ አልቻልንም?

አሁንም እድሉ ስላለን፤ ጥቃቅን የምሁራን ክበቦችን ሙጥኝ ብሎ አማራ፣ ትግሬ፣ ወላይታ፣ አኟክ፣ ሶማሌ፣ ኦሮሞ፣ የሚሉ መለያዎችን አንግበን ከመራመድ ይልቅ፣ በኢትዮጵያ ሠፊ ድንኳን ውስጥ የሚኖሩ ዜጎቿ ሁሉ ከድህነት፣ ከኋላ ቀርነት፣ ከጭቆና ነጻ ወጥተው፣ ድምጻቸው ተሰምቶና ተከብሮ የሚኖሩባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንዴት እንመስርት? የሚለው ጥያቄ ላይ ብንረባረብበት እመርጣለሁ፤ እመኛለሁ፡፡

ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ኃላፊታቸውን ተወጥተዋል ወይ?

ይኼ በጣም አስቸጋሪ ጥያቄ ነው፤ ራሴንም ይመለከታል። በኔ እምነት፣ የኢትዮጵያ ምሁራን ከሌላው ህዝባችን የምንለይበትም፣ የምንዛመድበትም ሁኔታዎች አሉ፡፡ የምንለይበት ዋና ምክንያት፣ በልዩ ልዩ ሞያዎች ከፍተኛ ስልጠናና ትምህርት ስላገኘን የማስተማር፣ እንዲሁም በግልና በመንግሥት ስራ የመሰማራት እድል አግኝተን፣ በሞያችን ለመወዳደር ስለምንችል፣ የበለጠ አርቆ የማሰብ እድል ይኖረናል፡፡ በተመሳሳይ፣ ይህ እድል ለአገርና ለሕዝብ ያለብንን ኃላፊነት ክብደት ከፍ ያደርገዋል፡፡ ወደድንም ጠላንም የወጣንበትን ሕብረተሰብ ልንረሳውአንችልም፡፡ ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ በምንሄድበት ሁሉ ከእኛው ጋር ይዞራሉ ብልአልሳሳትም፡፡

የኢትዮጵያ ምሁራን ልክ እንደሌላው የሕብረተሰብ ክፍል፣ የተቻለንን ማድረጋችን ምንም አይካድም፡፡ ምሁሩም ሆነ ሌላው፣ ለአገሩና ለሕዝቡ መስዋዕት ሆኗል፤ እርስ በርሱም ተገዳድሏል፡፡ ባለመስማማቱ የተነሳ፣ ብሄራዊ የተቋም፣ የፖሊሲና የአመራር ክፍተቶች ፈጥሯል፡፡ አለን ፔይተን እንዳለው አገራችን “ተሰብራች” ካልን ማንም ሊጠግንን አይችልም፤ ሃላፊነቱን መሸከም አለበን።

ምሁሩም ሆነ ሌላው፣ “ፖለቲካ ኮረንቲ ነው” ብሎ በቤቱ ከተዘጋ ፋይዳ ያለው ነገር አይሰራም፡፡ የምሁራን ኃላፊነት ሲባል አግባብ የሆነ መስፈርት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

የብዙ ዘውጎችና ኃይማኖቶች ባለቤት በሆነችው ኢትዮጵያ፣ ምሁራን በጋራ ችግሮችን አጢነውና የሚያዋጣውን ዘላቂና ፍትሃዊ አማራጭ ጸንሰው፤ ለሁሉም ዜጎች የሚጠቅም የፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እድገት፣ የሕገ መንግሥት አማራጭና የዴሞክራሲ አቅጣጫ ለማቅረብ አልቻልንም፡፡ ሁሉም በየፊናው፣ ‹‹በቋንቋና በዘውግ የተመሰረተውን ሕገ መንግሥትን መከተል አገር አፍራሽ ነው፤ መቀየር አለበት›› የሚለው በአንድ በኩል፤ ‹‹እንደዚህ ያለ የብሄር፣ ብሄረሰቦችንና ሕዝቦችን መብትና እኩልነት፣ ራሳቸውን የመግዛት መብት ያከበረና ያስከበረ የፌድራል ስርዓት አይተን አናውቅም፤ ይህ ሕገ መንግሥት ይከበር፤ ችግሩ የአፈጻጸም እንጂ የመርህ ጉዳይ አይደለም›› የሚሉት በሌላ በኩል ሆነው፣ ትግል እያካሄዱ ናቸው፡፡

በእኔ ግምገማ፣ የኢትዮጵያ ምሁራን ዋናና ወቅታዊ ሚና፣ ይሄን አደገኛ ሁኔታ ቁሞ ማየት ሳይሆን፣ ሁሉም የጋራ ውይይት ማድረግና መፍትሄ ማቅረብ ይጠይቃል፡፡ ከአሁን በኋላ ችግሮችን በጦርነት እፈታለሁ የሚል ካለ፣ አካሄዱ ቂልነት ብቻ ሳይሆን፣ ፍጹም ድንቁርና ነው የሚሆነው፡፡ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የተፈተነው የግጭት መንገድ ሊያዋጣ አይችልም፡፡ ምሁራን ማተኮር ያለብን ከዚህ ላይ ነው፡፡ ችግሩ የሃሳብ ልዩነቱ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫም አይደለም፤ የመካከለኛ መንገድ ለመፍጠር አለመቻሉ ነው፡፡

ሁሉም በራሱ ቡድን፣ በራሱ ዘውግ፣ መደብ፣ ኃይማኖትና ሌላ መለያ ትግልን የሚያካሂድ ከሆነ፣ ሂደቱ ካለፈው የፖለቲካ ታሪካችን አይለይም፤ አደገኛ ነው፡፡ አገሪቱን መልሶ ወደ አሮንቃ ሊያሸጋግራት እንደሚችል ደፍረን የመናገር ግዴታ አለብን፡፡ የምሁራን ሚና የተለያዩ ኃይሎችን ማቀራረብ ጭምር ነው፡፡

ስለዚህ፣ በተለይ በ21ኛው መቶ ክ/ዘመን ከተከሰቱት ተግዳሮቶች አንጻር ስመራመረው፣ የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ትስስርና ውድድር፣ የአየር ጠባይ ለውጥ፣ የሕዝብ ቁጥር እያደገ መሄድ፣ የስራ እድል እጥረት፣ የከተሜነት መስፋፋት ወዘተ. ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ምሁራን ኃላፊነታችን ተወጥተናል ለማለት አልችልም፡፡ ይህንም ሃቅ ለመቀበል የማንችል ብዙ ነን፤ ‹ችግር የለም› ካልን መፍትሄ ለማግኘት አንችልም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የምናጠፋው ህዝብን ሳናማክር መፍትሄ መስጠቱ ላይ ነው፡፡

አልበርት አይንስታይን የተናገረውን ምክር ስራ ላይ ለማዋል የምንሞክር ጥቂቶች ነን፤ ማለትም፣ በችግሩ ላይ የጋራ ግንዛቤ ይኑረን፤ ይህ ከሆነ መፍሄው ቀላል ይሆናል፡፡ “If I had an hour to solve a problem, I’d spend 55 minutes thinking about the problem and 5 minutes thinking about solutions..” ይላል አንስታይን፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልገናል፡፡ ከራሳችን ሕዝብ ልምድ ብንማር የተሻለ ውጤት እናገኝ ይሆናል፡፡ “

ህዝብ ለውጥ አምጥቷል

ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ሥልጣን ከያዙ ሰባት ወራት አልፏቸዋል፡፡ እሳቸው ሥልጣን ከማያዛቸው በፊት፣ የተከሰተውን እጅግ የሚያስፈራ ሁኔታን ማጤን አስፈላጊ ነው፡፡ ብዙ ጥናቶችና ምርምሮች በተከታታይ ያስተጋቧቸው የነበሩትን ዘገባዎች መርሳት አልችልም፡፡ ለምሳሌ፣ ጥር 2012 እ.ኤ.አ የአሜሪካ መንግሥት የደህንነት ተቋም ባደረገው ጥናት መሰረት “በ2030 ኢትዮጵያ ወድቀዋል ከሚባሉት አገሮች መካከል (እንደ ሶርያ፤ ሶማልያና ደቡብ ሱዳን) አንዷ ትሆናለች” የሚል ድምዳሜ ደርሶ ነበር፡፡ ለዚህ ብዙ ምክንያቶች ነበሩ፤ አፈናው፣ ግድያው፣ የኮማንድ ፖስቱ፣ የስራ እድል መጥፋቱ፣ ስደቱ፣ ሌብነቱ፣ ከሕግ ውጭ ከአገር የሚሸሸው የአገሪቱ ኃብት፣ የሰብአዊ መብቶች መጣስ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ምንም እንኳን ከግለሰቡ ጋር ባልስማማም፤  Kunwall Abbas (“Why Ethiopia is a failed state, December 2012” በሚል ዘገባው መንግሥትና የሕግ የበላይነት እንደሌለ፣ የስራ እድል፣ ምግብና የመንግሥት አገልግሎት እንደሌለ አትቶ ነበር፡፡ ሌሎችም ሚዛናዊ የሆኑ ትንተናዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ፣ የተባበሩት መንግሥታት የንግድ ድርጅት (UNCTAD) “ኢትዮጵያ የእድገቷን ጥልቀት ለማስፋት ከፈለገች ከፍተኛ የመዋቅር ለውጥ ታድርግ፤ የግሉ ክፍል መስፋት አለበት፣ የገጠሩ ኢኮኖሚ ዘመናዊ መሆን አለበት” ማለቱ ይታወሳል፡፡

በጥቅሉ፣ ኢትዮጵያ ሶስት የማይካዱ እውነታዎች ውስጥ ነበረች፤

  1. የመፈራረስ እድሏ ከፍተኛ ነበር፣
  2. ወደ የእርስ በርስ ጦርነት እያመራች ነበር፣
  3. የውጭ ጠላቶቿ ሁለቱም እንዲሆኑ የተቻላቸውን እያደረጉ ነበር፡፡

ስለዚህ፣ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አገሪቱን ለመምራት እድል ያገኙበት “የመሪ ያለህ፤ የአገር ወዳድ ያለህ” በሚባልበት ጊዜ ነው ብል አልሳሳትም፡፡

ይህን ዕድል ተጠቅሞ ለአገርና ለወገን መቆም ሁልጊዜ አይገኝም፤ እድሉን የሚጠቀሙት መሪዎች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ይህን እድል ያመቻቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተለይ መስዋዕትነት የከፈለው፣ አሁንም በየቦታው የሚታገለው ወጣት ትውልድ መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡

ሕዝብ ለመብቱ ባይነሳ ኖሮ፣ ዐቢይ፣ ለማ መገርሳ፣ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ደመቀ መኮንንና ሌሎችም ተደፋፍረው የህወሓትን የበላይነት እየናዱ ሊወጡ ባልቻሉ ነበር፡፡ የእነ ዐቢይ ጥንካሬ የሚያንጸባርቀው የሕዝቡ፣ በተለይ የወጣቱ ድጋፍና እምቢተኛነት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ የሕዝቡ እምቢ አልገዛም ባይነት ይኼን ሊቀለበስ የማይችል፤ ሕዝብን መሰረትና ደጀን ያደረገ ለውጥ አምጥቷል፡፡

የእኔም ግዴታ ከዚህ ታላቅ ሕዝብ ጋር አብሮ መጓዝ ነው፤ ለዚህ የተቋማት ተሃድሶ ወሳኝ መሆኑን በሚሰለች ደረጃ እደጋግመዋላሁ።

Revised slightly November 21, 2018

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here