ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው በእውቀትና በትእግስት መስራት ያስፈልጋል- አቶ ለማ መገርሳ

0
23

ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው በእውቀትና በትእግስት መስራት ያስፈልጋል- አቶ ለማ መገርሳ
************************************************************

አሁን የተገኘው ድል በበርካታ ዜጎች ከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘ በመሆኑ በዚሁ ለማስቀጠል በእውቀትና በትዕግስት መስራት እንደሚያስፈልግ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ገልጸዋል፡፡

አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ /ኦኤምኤን/ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱን ለማስመረቅ በተዘጋጀው ስነ ስርዓት ላይ እንደተናገሩት ከአሁን በኋላ የወጣቱ ዋንኛ ዓላማም ለልማትና ለብልጽግና መስራት መሆን አለበት፡፡

ጃዋር መሃመድን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ዜጎት ለህዝቡ ነጻነትና መብት ሲሉ በስደት ከሚኖሩበት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ከክልሉ ጋር ለመስራት በመወሰናቸው ምስጋና እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

የህዝቡ ትግል ፍሬያማ እንዲሆን ጃዋር መሃመድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉ ግለሰቦች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ በመሆኑ ልናመሰግነው ይገባል ነው ያሉት፡፡

ኦኤምኤን ትልቅ ስራ ሲያከናውን እንደነበር እና የኦሮሚያ ህዝብ ያገኘውን የተስፋ ብርሃን ይበልጥ እንዲፈካ ለማድረግ ከሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ጋር እንደሚሰራ ተስፋ አለኝ ብለዋል አቶ ለማ መገርሳ፡፡

እንደ አቶ ለማ መገርሳ ገለጻ ከአሁን በኋላ በፖለቲካ ምክንያት ህዝቡ መጋጨት እና መበጣበጥ የለበትም፤ ይህ ደግሞ እንዳይሆን የፖለቲካ አመራሮች የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ሊወጡ ግድ ይላቸዋል፡፡

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ /ኦኤምኤን/ ዳይሬክተርና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ጃዋር መሃመድ በበኩሉ ኦሮሚያን ማልማት፤ የሰላም ምድር ማድረግ፤ የዲሞክራሲ ድርዓት እንዲስፋፋ በአንድነት፤ በመስማማት መስራት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

በመሆኑም በአንድነትና በፍቅር ጠንክሮ በመስራት የህዝቡን ሰላምና ብልጽግና የማይፈልጉትን ሃይሎች በንቃት መጠበቅ እንሚገባም ተናግሯል፡፡

በመሆኑም ማንኛውም አካል ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ይጠበቅበታል ነው ያለው፡፡

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችም ወደ ሀገራቸው በመመለስ በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን እንዲያካሄዱና የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የአማራ እና የኦሮሚያን ህዝብ አንድነት እና ወንድማማችነትን በማጠናከር ረገድ ኦኤምኤን ትልቅ እስታዋጽኦ ነበረው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል የኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ናቸው፡፡

አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለውጥ አንድነትን፤ ፍቅርን፤ መተባበርን፤ ይቅርታን በህዝቡ ዘንድ በማስፋት ቂም በቀል፤ ጭቆናና በደልን ቦታ ያሳጣ ነው ብለዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here